RSS

ኮምቦልቻ (ወሎ) የተደረገውን የአንድነት፣ የሶደቃ፣ የዳዕዋና የዱዓ ፕሮግራም ቅኝት (ክፍል 1) by brother Marwolela Mekonnen

23 Apr

ኮምቦልቻ (ወሎ) የተደረገውን የአንድነት፣ የሶደቃ፣ የዳዕዋና የዱዓ ፕሮግራም ቅኝት (ክፍል 1) by brother Marwolela Mekonnen(www.facebook.com/marwolela)

ኮምቦልቻ በደቡብ ወሎ መስተዳድር ዞን ስር ያለች ከተማ ስትሆን የዛሬን አያርገውና የታላላቅ ዑለማዎች ማዕከል ነበረች፡፡ ብዙዎች ይህችን ከተማ የአህባሽ መፈልፈያ እንደሆነች ይስማማሉ -ለነዋሪዎቿ በርግጥ ይህ እጅግ አሳማሚ እውነት ቢሆንባቸውም፡፡ ሌላው የሐገሪቱ ክፍል ሰላም ውሎ እያደረ በነበረበት ጊዜ እንኳ ከተማዋ ብቻዋን ከልጆቿጋር ስትታመስ ከርማለች – በአህባሽ፡፡ አክራሪ፣ አሸባሪ፣ የአልሸባብ አባላት፣ ለአልቃዒዳ አሸባሪዎችን የሚመለምሉ፣ ወዘተ ወዘተ በሚሉ መሰረተ ቢስ ውንጀላዎች ልጆቿ በተደጋጋሚ ለበርካታ ወራቶች ለእስር ሲዳረጉ ኖረዋል፡፡ የዚህ ሁሉ እስር ኃላፊና አዛዥ ደግሞ ከዚህ ቀደም የነበረው የከተማዋ ከንቲባ ነው፡፡ በርግጥ የአህባሾች ድጋፍ እንዳለው ቢታወቅም፡፡ ግለሰቡ በፈለገው ጊዜና ሁኔታ የፈለገውን የማሰርና የማሳሰር ስልጣን ማን እንደሰጠው ባይታወቅም በፍርድ ቤት ነጻ ናቸው ተብለው የተለቀቁ ንጹሃን ዜጎችን ጭምር ከፍርድ ቤቱ በር ላይ እያፈሰ ሲያስር ከርሟል፡፡ . . . እንግዲህ ኮምቦልቻ ካቅሟ በላይ የሆነውን የአህባሽ ወረርሽኝ ለመመከት ብቻዋን ስትዳክር የነበረች ከተማ ለመሆኗ ይህ እንደማሳያ በቂ ይመስለናል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በስፋት በሌላ ዝግጅት እንመለስበታለን፡፡ ይህን ለመንደርደሪያ ያህል ያዙና ወደ ዋናው ርዕሳችን እንመለስ፡፡
በከተማዋ ይህን የሶደቃና የአንድነት ፕሮግራም ለማዘጋጀት ከታሰበ የቆየ ቢሆንም ቀኑን ለመወሰን ግን አልተቻለም ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ቦታና ጸጥታ ነው፡፡ ኮምቦልቻ ላይ አንድ ግለሰብ (አህባሽ) ካልሆነ በቀር በየትኛውም መስጂድ ዳዕዋ ማድረግ የተከለከለ ነው – የተብሊግ ጀመዓም ጭምር፡፡ ህዝቡ ከዓመት እስከ ዓመት የሚያደምጠው የዳዕዋ ፕሮግራም የለውም፡፡ የተብሊግ ጀመዓ በከተማዋ ሲዘወዘወር ከተገኘ ፖሊስ ያለ ምንም ህጋዊ መሰረት ለእስር ይዳርጋቸዋል፡፡ ከሌላ ከተማ መጥቶ ዳዕዋ ማድረግ በኮምቦልቻ ያሳስራል፡፡ ማንኛውም ዓይነት ኢስላማዊ እንቅስቃሴ በፖሊስ ኃይል ይሰናከላል፡፡
ከዚህ ልምድ በመነሳት ነበር የፕሮግራሙን ቀን መወሰን አስቸጋሪ የሆነው፡፡ በመሀሉ የወልዲያ የአንድነትና የሶደቃ ፕሮግራም ላይ የተሳተፉ የኮምቦልቻ ነዋሪዎች እነሱም በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚያዘጋጁ ለዚያ ፕሮግራም ታዳሚዎችና ለመላው ማህበረሰብ አወጁ፡፡ ይህም ዜና ኮምቦልቻ ላሉና ወልዲያ ላልተጓዙ ወንድሞችና እህቶች በስልክ ሲነገራቸው በመጀመሪያ ለማመን ተቸገሩ፡፡ ምክንያቱም ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር በጣም አስቸጋሪ ከመሆኑም በተጨማሪ ጊዜው በጣም አጭር ነበር፡፡ ከተወነሰነ መደነባበር፣ ድንጋጤና ጭንቀት በኋላ ሁሉም በቆራጥነት ዝግጅቱን ወደ ማሰናዳቱ አመራ፡፡
ወደ ዝግጅቱ ሲገባ ሁለት መሰረታዊ ነገሮች አሳሳቢ ነበሩ፡፡ አንደኛው ቦታ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ጸጥታ ነው፡፡ ጸጥታን በተመለከተ በሁለት መክፈል ይቻላል፡፡ አንደኛው ፕሮግራሙ እንዳይካሄድ የሚፈልጉ ጥቂት የአህባሽ ወጠጤዎች ሊፈጥሩ የሚችሉት ግርግር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ እንደ ከዚህ ቀደሙ በጸጥታ ኃይሎች ሊወሰድ የሚችለው የአፈናና የእስር ጉዳይ ነው፡፡
ቦታውን በተመለከተ የከተማው ህዝብ የገነባውና ዒድ የሚሰገድበት የኻሊድ መስጂድ ከዚያም በተለምዶ በርበሬ ወንዝ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ያለውን የኳስ ሜዳ እንዲፈቀድ ጥረት ቢደረግም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ይህ ቦታን የማሰፈቀድ ሂደት እስከ ቅዳሜ 11፡00 ሰዓት ድረስ ዘልቆ በመጨረሻ ጊዜው ስለሄደና ወደ ስራ መገባት ስለነበረበት በመጅሊስ ቁጥጥር ስር ባልሆነው የተቅዋ መስጂድ ቅጥር ግቢ ላይ መሰናዶው ተጀመረ፡፡ ለእሁድ ፕሮግራም ቅዳሜ 11፡00 የቦታ ዝግጅት መጀመር የሚከብድ ቢመስልም በአላህ (ሱወ) አገዛና በህብረተሰቡ (ክርስቲያን ወገኖችም ጭምር) ብርታት በፍጥነት ሊጠናቀቅና ዝግጁ ሊሆን ችሏል፡፡ አልሐምዱሊላህ፡፡
ከዚህ ጎን ለጎን የከተማው ፖሊስ የፕሮግሙን አስተባባሪዎች በመጥራት ከፍተኛ ዛቻና ማስፈራሪያ ያደረገ ቢሆንም ከአስተባባሪዎቹ የተሰጠው ቆራጥ መልስ ፕሮግራሙን ማስቀረት እንደማይችል በቂ ግንዛቤ ሰጥቶታል፡፡ ለዚህም የፕሮግራሙን አስተባባሪዎች ማሰርና ሌሎች ፕሮግራሙን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበት ተገንዝቦ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡
በፖሊስ ከተወሰዱ እርምጃዎች ውስጥ ለፕሮግራሙ ግብዓት የሚሆኑ ነገሮችን በሙሉ ማገድ የሚል ይገኝበታል፡፡ በዚህም መሰረት እንጀራ ይጋገርበታል ተብሎ የታሰበ ቤት ሁሉ እንዲፈተሸ፣ ከተገኘ እንጀራው ተወርሶ ግለሰቡን ማሰር፡፡ ይህንም ለማድረግ ጭስ በሚታይበት ቤት ውስጥ ሁሉ ፍተሻ ተደርጎ የተወሰኑ ግለሰቦች ታስረዋል፡፡
ሁለተኛው የፖሊስ እርምጃ ለፕሮግራሙ ማሰኬጃ የተገዙ በሬዎችን መውረስ የሚል ሲሆን በሬዎቹ ሐሙስ ቀን ከሚሴ ከተማ መገዛታቸውን መረጃ ስለነበራቸው ከዛ ቀን ጀምሮ ከፍተኛ አሰሳና ክትትል ሲያደርጉ ሰንብተዋል፡፡ የከተማዋ ትራፊኮች በመኪና ተጭኖ ወደ ከተማዋ የሚገባ ከብት ካለ እንዲይዙ የታዘዙ ሲሆን ሌሎች ፖሊሶች ደግሞ ከብት ሊያድርባቸው ይችላሉ የተባሉ የግለሰብ ግቢዎችን ጨምሮ በአቅራቢያ ያሉ ጫካዎችን ሁሉ ቀን ከሌት በመፈለግ ሲባዝኑ ከርመዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሬዎቹ እስከ ቅዳሜ ድረስ ሀርቡ ከተማ ቆይተው ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በአላህ (ሱ.ወ) ፈቃድ በሰላም ገብተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ለፕሮግራሙ ከደሴና ከባቲ ይመጣ የነበረን አንድ አይሱዙ ሙሉ ውሃና ሁለትና ከዚያ በላይ መኪና የተጫነ ሳርና ቄጠማ ወደ መጡበት እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡
ለከተማዋ ኢማሞችና ሙአዚኖች በተሰጣቸው መመሪያ መሰረት በሁሉም ጁምዓ በሚሰገድባቸው መስጂዶች ጁሙዓ ሊሰግድ ለተሰባሰበው ሙስሊም ህብረተሰብ “እሁድ በተዘጋጀው የወሃቢዮች ሶደቃ ላይ (“ጣልቃ ያልገባው”) መንግስትና መጅሊስ ስላልፈቀዱት እንዳትገኙ በአላህ ስም እንጠይቃለን” የሚል መመሪያ ከማስተላለፋቸው በተጨማሪ በከተማዋ በሚተላለፈው የኮምቦልቻ ኤፍ ኤም ሬዲዮ አማካኝነትም ይህ መልዕክት በተደጋገሚ ተስተጋብቷል፡፡

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on April 23, 2013 in Uncategorized

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: