RSS

ኮምቦልቻ (ወሎ) የተደረገውን የአንድነት፣ የሶደቃ፣ የዳዕዋና የዱዓ ፕሮግራም ቅኝት (ክፍል 2) by brother Marwolela Mekonnen

23 Apr

by brother Marwolela Mekonnen(www.facebook.com/marwolela)

ኮምቦልቻ (ወሎ) የተደረገውን የአንድነት፣ የሶደቃ፣ የዳዕዋና የዱዓ ፕሮግራም ቅኝት (ክፍል 2)

በክፍል አንድ ጥንቅር ፕሮግራሙን ለማሰናዳት የነበረውን ውጣ ውረድ ለመቃኘት ሞክረናል፡፡ ቀጣይ ሂደቶችን ደግሞ በዚህ ጽሁፍ እንዳስሳለን፡፡ በተለያዩ ቦታዎችና ከተሞች የተደረጉት የሶደቃና የአንድነት ፕሮግራሞች የራሳቸው የሆነ የተለየ አጋጣሚዎችን የፈጠሩ ቢሆንም የኮምቦልቻው ደግሞ በዓይነትም በይዘትም ልዩና የማይረሳ ታሪክን አስተናግዷል፡፡ ከነዚህ ልዩና አይረሴ ክስተቶች ውስጥ የተወሰኑትን ለመጥቀስ እንሞክር፡፡
ከክስተቶቹ ውስጥ በክፍል አንድ በቀረበው ጥንቅር ላይ በስሱ ከተጠቀሱት በአንዱ እንጀምር፡፡ ለእርድ የተገዙት 9 በሬዎችና 10 ሙክቶች ታርደው የታረደው ስጋም ለመከተፍ የፈጀው ሰዓት ከ1፡30 እና 40 ደቂቃ አይበልጥም ነበር፡፡ የተጠባውን ስጋ በመክተፉ በኩል ሴቶቹ በሚገርም ፍጥነትና ቅንጅት ሰርተው የጨረሱበት ጊዜ ለማመን ይከብድ ነበር፡፡ የሰማይ መላዕክቶች (መለይካዎች) ለጂሃድ ብቻ ሳይሆን ለስጋ ከተፋም እገዛ ያደርጋሉ እንዴ? አስብሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሴቶቹ በኩል የተስተዋለው ለዲን የመቆርቆር ስሜት በቃላት ለመግለጽ ይከብዳል፡፡ የነበረው ውጣ ውረድ፣ እልህ አስጨራሽ ትግልና ትርምስ የፈጠረባቸውን ተጽዕኖ መቋቋም ተስኗቸው ተስተዉሏል፡፡ ብዙ ማድረግ አስበው አንድም የማድረግ አቅምና ዕድል ስላልነበራቸው የውስጣቸውን ንዳድ በእንባቸው “አበረዱት”፡፡ ይህ ቃል (“አበረዱት”) ሁኔታውን ይግለጸው አይግለጸው እርግጠኛ አይደለንም፡፡ ለዚያም ነው በትዕምርተ ጥቅስ ውስጥ ማስገባታችን፡፡ ብቻ እጆቻቸውና ዓይኖቻቸው እኩል በስራ ተጠምደው ነበረ – አንዱ በመክተፍ ሌላው በማንባት፡፡ ጀሊሉም የልባቸውን አይቶ ጉዳዩን አሳካላቸው፡፡ ለዚያውም ከጠበቁትና ካሰቡት በላይ አሳምሮ፡፡ የጌታና የባሪያ ጥምረት ስኬት ማረጋገጫ ይሏል እንዲህ ነው፡፡ አስብ ወይም ከጅል፣ ከዚያም ሰበቡን አድርስ፣ ከዚያም ፊትህንና ጉዳይህን ወደ ጌታህ መልስ፤ ከዚያ በኋላ ውጤቱን በተስፋ ጠብቅ፡፡ በውጤቱ መሰረትም አመስጋኝ ባሪያ ሁን፡፡
. . . . . . . . . . . . . . . . .
ወደ ቀጣይ የፕሮግራሙ አጠቃላይ ሂደት ስንሸጋገር ደግሞ ከዚህ የተለየ ነገር ይጠብቀናል፡፡ ፕሮግራሙን የማዘጋጀቱ ሂደት በጦፈበት የቅዳሜ አመሻሽ አንድ አስደንጋጭ ዜና ተሰማ፡፡ ይህም የፌደራል ፖሊስ በከተማዋ መግቢያ ቦታዎች ላይ በመሆን ከፍተኛ ፍተሻ እያደረገ መሆኑና ለዚህ ፕሮግራም ብለው የሚመጡ ግለሰቦችን መመለስ ብሎም ማሰር መጀመሩ ነው፡፡ ይህ ስጋት በተለይ ከአዲስ አበባ የሚመጡትን ዳዒዎች እንዳይመልሳቸው በማለት ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ገባ፡፡ በዚህ መሀል ወግዲ ለሚዘጋጀው የአንድነትና ሶደቃ ፕሮግራም ላይ ለመገኘት ሲጓዙ የነበሩት ሼይኽ መሐመድ ሃሚዲንና ኡስታዝ ባህሩ ዑመር ሐርቡ ከተማ መታገታቸው ተሰማ፡፡ በዚህ ጊዜ ህዝቡ ወደ ባሰ ጭንቀትና ሀዘን ተሸጋገረ፡፡ በቦታው ላይ መደናገጥ፣ መረበሽና መጨናነቅ ነገሰበት፡፡ ወደ ኮምቦልቻ የሚመጡትም ዳዒዎች ተመሳሳይ እጣ እንዳይደርሳቸው ተሰጋ፡፡ ስጋት ብቻውን መፍትሄ አይሆንምና ምን እናድርግ ወደሚል ሃሳብ ተሸጋገረ፡፡ ለዚህም በርካታ ሃሳቦች ፈለቁ፡፡ የተወሰኑት ወደ ትግበራ ተሸጋግረው ውጤቱን በዱዓ መጠበቅ ተያዘ፡፡ ክብርና ምስጋና ለጀሊሉ ይሁንና ዳዒዎቹ ያለምንም የከፋ ችግር ኮምቦልቻ ደረሱ፡፡ ዳዒዎቹ ወደተዘጋጀላቸው ማረፊያ እስከደረሱበት ሌሊት 6፡00 ሰዓት ድረስ የህዝቡ ጭንቀትና መረበሽ ከሚስተዋለው መቁነጥነጥና በልቅሶ የታጀበ ዱዓ ላይ በጉልህ ይስተዋል ነበረ፡፡
. . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . .
ፍተሻው በሶስቱም ወደ ከተማዋ የሚያስገቡና የሚያስወጡ ዋና ዋና መስመሮች ከ200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ተጧጡፏል፡፡ በአዲስ አበባ መስመር ሸዋሮቢት፣ ከሚሴ፣ ሐርቡ፣ ፎንተኒናና ጮሪሳ ላይ፤ በመቀሌ መሆኔ ከምትባልና ከአለማጣ አቅራቢያ ካለች አነስተኛ ከተማ ጀምሮ ዉጫሌ፣ ሐይቅ፣ ጀሜ፣ ሐረጎ፣ ደረቅ ወይራና ጠቢሳ፤ በባቲ በኩል ደግሞ ወርሰይ ላይ ነበር፡፡ የቅዳሜ ቀኑ ፍተሻ በጣም አስፈሪና ጠንካራ የሚባል ነው፡፡ ፈታሾቹ ላይ ይነበብ የነበረው የድንጋጤና የመደነባበር ሁኔታ ከፍተኛ የጸጥታ ችግር የተፈጠረ አስመስሎታል፡፡ ከዚያም አልፎ ከሌላ ፕላኔት የመጡ አካላትን የሚፈልጉም ይመስላል፡፡ ሲፈትሹ ደግሞ ኪስ ውስጥ የተገኘ ወረቀት ሳይቀር ይበረበራል፡፡ ምን ተብለው ቢነገሩ ይሆን እንደዚያ ዓይነት ድንጋጤና ፍርሃት ውስጥ የገቡት? በዚህ ዓይነቱ ፍተሻ በተለይ ከወልዲያ በኩል ለስራ ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱ ተጓዦች ጭምር በግድ ወደመጡበት እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡
በማግስቱ ዕለተ እሁድ ፕሮግራሙ ላይ ለመታደም ከየአቅጣጫው ይተም የነበረው ሙስሊም ማህበረሰብ በሶስቱም ቦታዎች ላይ ታገተ፡፡ ከአፋር፣ ከባቲ፣ ከገርባና ከደጋን ይመጣ የነበረው እጅግ በርካታ የህብረተሰብ ክፍል ወርሰይ ከምትባልና በግምት 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከምትገኝ ቦታ ሲታገቱ፣ ከአዲስ አበባ (ከአዲስ አበባ የመጡት ዳዒዎቹን ጨምሮ አብዛኞቹ ሌሊት 6፡00 ሰዓትና ከዚያ በኋላ ገብተዋል)፣ ከከሚሴ፣ ከሐርቡ የመጡት ደግሞ ፎንተኒና ከሚባልና በግምት 18 ኪሎ ሜትር ርቀት ካላት ቦታ፣ ከደሴ የሚመጡት ወደ አውቶቡስ መነኻሪያ ቢሄዱም ወደ ኮምቦልቻ የሚሄድ መኪና ባለመኖሩ (በመከልከሉ) 24 ኪሎ ሜትሮችን በእግራቸው መጓዝ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ የፀጥታ ኃይሎች በእግር የሚጓዙትንም ለማገድ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም ህዝቡ ዋናውን መንገድ በመተው በዱር በገደሉ ስለተጓዘ ለመከላከል አልቻሉም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከሐይቅ ከተማ እዚያው ሐይቅ ላይ ሲታገቱ ከወልዲያ የሚመጡት ደግሞ ውጫሌ ላይ ተገደው እንዲመለሱ ተደርጓል፡፡ ከነዚህ ውስጥ ሳንደርስ አንመለስም በማለት ከ114 ኪሎ ሜትር ርቀት (በአቋራጭ ሊቀንስ ይችላል) በእግር ጉዞ ከጀመሩት በርካታ ሰዎች ውስጥ ስድስቱ ፕሮግራሙ ከተጠናቀቀ በኋላ ከምሽቱ 12፡30 አካባቢ ቦታው ላይ ደርሰዋል፡፡ ከደሴ ህጻን ልጃቸውን ታቅፈው ይመጡ የነበሩ አንዲት እናትን ትከሻው ላይ የማዕረግ ኮከብ ያለበት መለዮ ለባሽ እንዲወርዱ ሲጠይቃቸው “አንተ ባለ ማዕረግ ነህ፡፡ ይህን ማዕረግህንም በሰራኸው ጀብዱ ነው ያገኘኸው፤ አሁን እኔን ልጅ አቅፌ 20 ኪሎ ሜትር በእግሬ እንድጓዝ ስታስገድደኝ ሰብዓዊነት አይሰማህም? ክብርህንና ማዕረግህን ዝቅ አያደርግብህም?” ሲሉት “ታ… ታ… ታ… ታዘን ነው” ብሎ ከቦታው ፊቱን ዞር ማድረጉ ተወስቷል፡፡
. . . . . . . . . . . . . . .
ሰዓቱ ከጠዋቱ 2፡30 ሆኗል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች ሌሊቱን ሙሉ በስራ ቢያሳልፉም የድካም ስሜት አይስተዋልባቸውም፡፡ እንደውም እንግዶቻቸውን ለማስተናገድ በከፍተኛ ጉጉት እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ የእንግዶቻቸው በየቦታው መታገድ ውስጣቸውን ሰላም ቢነሳውም ከመስራት ወደ ኋላ አላሉም፡፡ በከተማዋ ውስጥ ምንም ዓይነት የትራንስፖርት አገልግሎት የለም፡፡ ስብሰባ ተገኙ በሚል ስራ እንዲቆም ተደርጓል፡፡ ይሁን እንጂ ገና ከማለዳው ከከተማ ውጪ የሚመጡ እንግዶች በታገቱበት ሰዓት ለእንግዳ ማረፊያ የተዘጋጀው ቦታ ፕሮግራሙን ለመከታተል በመጣው የከተማዋ ህብረተሰብ ተሞልቷል፡፡ ይህ አስደሳችም አስደንጋጭም ሆነባቸው፡፡ ፕሮግራሙ ላይ እንዳይገኝ ስንት የተለፋበት ህብረተሰብ በነቂስ መምጣቱ አስደሳች ቢሆንም ገና በማለዳው ቦታ መጣበቡ አርፍዶ ለሚመጣው ህብረተሰብና በየቦታው ለታገቱ እንግዶች የሚሆን ቦታ መጥፋቱ ደግሞ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ቢሆንም አሁንም ተጨማሪ ስራ መሰራት አለበት፡፡ ከደሴዎቹ ገብርኤልና መካነ ኢየሱስ አብያተ ክርስቲያናት ከመጡት ሁለት ሰፋፊ ድንኳኖች በተጨማሪ ባሉ ክፍት ቦታዎች ላይ ከመስጂዱ ቅጥር ግቢ ውጪ ሁሉ ዳስ ተጣለ፡፡ ያም ሆኖ ግን ቦታውና እንግዶቹ በፍጹም ሊመጣጠኑ አልቻሉም፡፡
በሁሉም አቅጣጫ የታገተው የህብረተሰብ ከፍል አልመለስም በማለቱ በተለያየ ሰዓት የተነሱት አንድ ላይ ተጠራቀሙ፡፡ መኪኖቹን ቢመልሷቸውም በእግራችን እንገባለን እንጂ አንመለስም በማለት ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር የተፋጠጡ ሲሆን በመጨረሻም የተወሰኑ ግለሰቦችን ኃላፊነት እንዲወስዱ ካስፈረሙ በኋላ እንዲገቡ ፈቅደውላቸዋል፡፡ ይህ አንድ ላይ የተሰባሰበ ህብረተሰብ በሶስት ዋና ዋና መስመሮች ወደ ከተማዋ ሲገባ ያሰማ የነበረው ተክቢራና መፈክር ያልታሰበ ሌላ የፕሮግራም ድምቀት አስገኝቷል፡፡ የኮምቦልቻ ነዋሪ ሆነው በኢማሞች ትዕዛዝ፣ በፍርሀትና በተለያየ ምክንያት ወደ ፕሮግራሙ ለመሄድ ፍላጎት የሌላቸውን ጭምር ሃሳብ አስቀይሯል፡፡ በእግር ተጉዘው ፕሮግራሙ ላይ ከታደሙ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ህጻናት፣ አረጋዉያን፣ እናቶችና የአካል ጉዳተኞች ይገኙበታል፡፡
ይህ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለበት ፕሮግራም ድምቀት ለጉድ ነበር፡፡ ገና በማለዳው ቦታው ላይ የተገኘው ህዝብ የፕሮግራሙን መጀመር በጉጉት እየተጠባበቀ እንዳለ ከታዳሚው የፊት ገጽታ ላይ ማስተዋል ይቻላል፡፡ መድረኩ ባዶ ቢሆንም ቅሉ ዓይኖቹ ከመድረኩ ላይ ተክሎ ካሁን ካሁን ተጀመረ በሚል ጉጉት ተቀምጧል፡፡ በዚህ ወቅት የነበረው የህዝቡ ሁኔታ አንድ የራበው ህጻን ምግብ የሚበሉ ሰዎች ፊት ተቀምጦ ካሁን ካሁን ያጎርሱኛል እያለ እንደሚጓጓው ዓይነት ነው፡፡ እርግጥ ነው የከተማዋ ህብረተሰብ ከፍተኛ የዳዕዋ ጥማት አለበት፡፡ ይህ ፕሮግራምም ይህን ጥማት ይቆርጥልኛል ብሎ ተማምኗል፡፡ ኮምቦልቻ የዚህ ዓይነት ፕሮግራም አይታም ሰምታም የምታውቅ አይመስልም፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ኡስታዝ ኢድሪስ አሊ (ከደጋን)፣ የኮሚቴው አባል የሆኑት ዳዒ ካሚል ሸምሱ፣ ኡስታዝ ያሲን ኑሩ፣ ሼይኽ መከተ ሙሄና ሌሎችም ያቀረቧቸው ፕሮግራሞች ህዝቡ ባይጠግባቸውም ተደስቶባቸዋል፡፡ በርግጥ ይህን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍሎ የመጣ ህዝብ በቀላሉ ይረካል ብሎ መገመት ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡
የነበረው አጠቃላይ የፕሮግራም ይዘት ከሌሎች ፕሮግራሞች ብዙም የተለዬ ባይሆንም ህዝቡ ዘንድ የነበረው ሞቅታና አቀባበል ግን በጣም የተለየ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በፕግራሙ ስለ ህገ መንግስት ተወስቶ ህዝቡ መብትና ግዴታውን እንዲያውቅ ሲደረግ በተለይም የህዝብን የመንቀሳቀስ ህገ መንግስታዊ መብት በመደፍጠጥ በሰዎች ላይ እንግልትና መጉላላት የፈጠሩ አካላት ለህግ እንዲቀርቡ ተጠይቋል፡፡ ይህ ሁሉ እንግልትና መጉላላት ሲደረግበት ህዝቡ ያሳየው ፍጹም ሰላማዊነትም አድናቆት አስገኚቶለታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ስለ አንድነትና ወንድማማችነት፣ ስለ መቻቻል፣ ስለ ምርጫ፣ ስለ ኮሚቴው ጉዞና ወደፊት ስለሚደረገው እንቅስቃሴ በስፋት ገለጻ ተደርጓል፡፡ ስነጽሁፍና የአንዳንድ ሰዎች የጉዞ ገጠመኞች የፕሮግራሙ ማጣፈጫዎች ነበሩ፡፡
. . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . .
በጉዞ ላይ ጥቂት የሚባሉ ችግሮች በቀር ሁሉም በመረዳዳትና በመደጋገፍ በሰላም ደርሰዋል፡፡ ችግር ካጋጠማቸው ውስጥ አንዲት ሁለት ልጆቻቸውን ይዘው የመጡ እናት በእግራቸው ላይ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ በተጨማሪም ሶስት እንስቶች መስጂድ ከደረሱ በኋላ ራሳቸውን ስተው ነበር፡፡ በተረፈ ግን ብዙ ርቀትን ተጉዘው የመጡና የደከሙ ቢሆንም በተለይ ሴቶቹ ቦታው ላይ ከደረሱ በኋላ የነበራቸው ሶብርና ጥንካሬ እንግዳ ተቀባዮችን አስደምሟል፡፡
በእግር ተጓዦቹ ቦታው ላይ መድረሳቸው ከመድረኩ ሲነገር አብዛኛው ሰው ያለቅስ ነበር – አንድም ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በመድረሳቸው ተደስቶ ሁለትም ኮምቦልቻ ላይ ያለው አፈናና የመብት ጥሰት እያቃጠለው፡፡
አንድ ያስገረመን ገጠመኝ ደግሞ ይህን ይመስላል፡፡ የሌላ እምነት ተከታዮች ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው በዝግጅቱ ላይ ጎላ ያለ ድርሻ የነበራቸው ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ግን “ኡስታዝ ያሲን ኑሩ ከመጣ እኛም እንመጣለን” ያሉ የኡስታዝ ያሲን ኑሩ “እንግዶች” መኖራቸው ነው፡፡
ካጋጠሙ አስደሳች ነገሮች ውስጥ ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ እኛ ጋር ከደረሱን የሚከተለውን እንበል፡፡ ከደሴ ሲመጡ የነበሩ እናት ጫማቸው በመበጠሱ ምክንያት አንድ ተመራቂ ተማሪ የራሱን የሱፍ ጫማ አውልቆ አልብሷቸዋል፡፡ እንዲሁም ለፕሮግሙ ተብሎ ከደሴ ይመጣ የነበረ አንድ አይሱዙ መኪና ሙሉ ውሃ በጸጥታ ኃይሎች እንዲመለስ ሲደረግ ከባቲና ከሐርቡ በሁለት መኪና የተጫነ ሳርና ቄጠማም (ስፍራው በዝናብ ስለጨቀየ ለማልበሻ) በተመሳሳይ ሁኔታ ተመልሷል፡፡ ይህ አሳዛኝ ዜና በተሰማበት ቅጽበት ሞንታርቦ ከደሴ ተጭኖ ቦታው ላይ ሲደርስ ያልገረመው አልነበረም፡፡ ላንዳንዱ ከሰማይ የወረደም የመሰለው አለ፡፡ ግን ሁሉም “እንዴት?” እንዲል አስገድዶታል፡፡ እኛም “እንዴት?” አልነው፡፡ “ኮማንደሩ መጥቶ ሲጠይቀኝ መስቀሌን ደረቴ ላይ ለቅቄ ‹ሙዚቀኛ ነኝ፤ የሰርግ ስራ ስላለብኝ ነው› አልኩት” . . .
በጉዞ ላይ እያሉ ያልታሰቡ ሰዎችን ማግኘታቸው ግርምት የፈጠረባቸው ወጣቶች በድንገት አንድ አረጋዊ ያገኙና “እንዴ ጋሽ አህመድ አንቱም?” ቢሏቸው ” ™úረ ባክህ ጀነት እኮ ነው” ማለታቸው ተወስቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መንገድ ላይ የነበራቸውን መተዛዘንና ወንድማማችነት ካሳዩ ገጠመኞች ውስጥ አንዱን እንጥቀስና እኛ እናብቃ፡፡ እናንተ ግን በተለይ የጉዞው ተዋናዮች ገጠመኞቻችሁን በስፋት እንድትጋብዙን በዚህ አጋጣሚ ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡ አንድ ሰው አንድ እግር ጫማ ይዞ ወደ መድረክ መጣ፡፡ ምን እናድርግ ተባለ፤ ይህ ጫማ መንገድ ላይ እያለሁ ከአንድ ወንድሜ የተዋስኩት ነው፡፡ አሁን ግርግር ውስጥ ፈልጌ ላገኘው ስላልቻልኩ በመድረኩ በኩል አመስግናችሁ እንድትመልሱልኝ ፈልጌ ነው በማለት አስደመመን፡፡
. . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . . .
በመጨረሻም ህዝቡ በፕሮግራሙ ከሚገባው በላይ የተደሰተበት መሆኑን ለማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን በእንግዶቹ ላይ ከደረሰው እንግልት አንጻር ተገቢ መስተንግዶ ማድረግ ባለመቻሉ ደግሞ በጣም አዝኗል፡፡ አህባሽ ካደናበራቸው ውሥጥም “እንዲህ ነው እንዴ?” ያሉም አልጠፉም፡፡ በከተማዋ ላይ ነግሶ የነበረውን የጥቂት አህባሾች አምባገነንነት ጋብ አድርጎታል፡፡ ለዚህም ይመስላል መፕሮግራሙ ማጠናቀቂያ ላይ አንድ ታዳሚ
የሰማህ አሰማ ያልሰማህም ስማ፣
አህባሽ ተዘርሯል ኮምቦልቻ ከተማ፡፡
የሚል ስንኝ የቋጠሩትና ለመድረክ ጀባ ያሉት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በፕሮግራሙ ይዘትና ሰላማዊነት የሌሎች እምነት ተከታዮች፣ የጸጥታና የደህንነት ሰዎች መገረማቸውንና በተለይ የጸጥታ ሰዎች ባልሆነ መረጃ ላይ ተመስርተው የፈጸሙትን እንዲመረምሩና ነገሮችን እንዲያጤኑ እንዳስገደዳቸው ተናግረዋል፡፡
የሆነው ሆነ፤ ያልሆነውም አልሆነ – ሁሉም በአላህ ፍቃድ ነው፡፡ አላህ የሁላችንንም ስራ ይቀበለን፡፡ አሚን፡፡

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on April 23, 2013 in Uncategorized

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: