RSS

ታሪካዊው እና ደማቁ የአንድነትና የሶደቃ ፕሮግራም በደሴ ከተማ በፉርቃን አደባባይ ተካሄደ

13 Apr

ታሪካዊው እና ደማቁ የአንድነትና የሶደቃ ፕሮግራም በደሴ ከተማ በፉርቃን አደባባይ ተካሄደ
(ሰኔ 12 2004)

ከተጠበቀው ታዳሚ በላይ የተሳተፈበት ይኸው ዝግጅት እስከ 11፡35 ድረስ ቆይታ የነበረው ሲሆን ተሳታፊውን እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ በመያዝ ማቆየት የቻሉ ፕሮግራሞች ቀርበውበታል፡፡ የደሴ ከተማ መሳጂድ ኢማሞችን ጨምሮ የ17ቱ ኮሚቴ አባላት የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል፣ ሸኽ መከተ ሙሔ፣ ካሚል ሸምሱ እና አሕመዲን ጀበል የፕሮግራሙ እድምተኞች ነበሩ፡፡ ከታላላቅ ዑለሞች መካከል ዶ/ር ከማል፣ ሸህ ማሕሙድ ሁሴን፣ የተባረክ መስጂድ ኢማም (ጀርመን መስጂድ አዲስ አበባ) እና ሌሎችም የተገኙ ሲሆን ኡስታዝ አብዱል መናን፣ የቄራ መስጂድ ምክትል ኢማም ወጣት ዳዒ ሰዒድ ዓሊ ወጣቱን ክፍል በመወክል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የፕሮግራሙን ድምቀት ካጎሉት መካከል በወጣቶች የቀረቡት የመንዙማ እንጉርጉሮ፣ የአንድነት ነሺዳ እና ከምሳ ረፍት በኋላ የቀረበው ዳሩል ሂጅረተይኒ የተሰኘው ቲያትራዊ ነሺዳ ይገኙበታል፡፡
በዕለቱ ዝግጅት የህዝቡን ስሜት ገዝተው የዋሉ ቁም ነገር አዘል መልዕክቶች የቀረቡ ሲሆን የመድረኩ ቀዳሽ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ታሪክን በማጣቀስ ወሎ “የሀበሻው አዝሐር” ትባላለች ሲሉ ሲጠሯት ወሎ የዒልምና የዑለማው ምንጭ ነች በዚህ በጣም ትኮራለች በተግባርም የታየ ታሪክ ነው፣ ተደብቆ አይቀርም በማለት እስልምና ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ቅርፅና ይዘት ወሎ ያበረከተችውን እና እያበረከተች ያለቸውን ታላቅ ሚና አስታውሰዋል፡፡ ይህ ከኛ አልፎ ለሌሎችም የበቃው የወሎ ብሎም የኢትዮጵያ ትሩፋት ተንቆ እና ተዋርዶ ዓረቢኛን በመናገራቸው ብቻ ይኸው ዛሬ ዓሊሞቻችንን ሊያሰለጥኑ መጥተዋል በማለት ምፀት በተሞላበት አንደበት ህዝቡን ያስገረመ ንግግራቸውን አሰምተዋል፡፡
የረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል ንግግርን በማድነቅና ወሎ ያፈራችው ግለሰብ ይህን የመሰለ ታሪክ አዘል ቁም ነገር ቢያወራ አይደንቅም፣ የሚጠበቅ ነው በማለት በአንድነት ዙሪያ የዓረቢኛ ንግግራቸውን በ ሸኸ ሐሰን ሐሚዲን አስተርጓሚነት ያቀረቡት ደግሞ ዶ/ር ከማል ነበሩ፡፡ በንግግራቸው ልዩ ትኩረት የሰጡት ሀሳብ በተለያዩ ምሳሌዎች እና መረጃዎች ተደግፎ የቀረብ ሲሆን “… ሊበታትኑን ይፈልጋሉ? ያውም ወደ ፊደላት! ወደ ሲ-ን እና ወደ ሷ-ድ! ሰለፊያዎች ሱፊያዎች እያሉ! እኛ ሙስሊሞች ነን! ” ሲሉም ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ከዚህ የመከፋፈል አደጋ ረሱን እንዲጠብቅ ዑለሞችም ይህን አስመልክቶ የቤት ስራቸውን እንዲወጡ አደራ ብለዋል፡፡
የመድረኩ ሞቅታ አካል ከነበሩት የመድረክ መልዕክቶች መካከል የእንጀራው ጉዳይ ይገኝበታል፡፡ ለሶደቃ ፕሮግራሞ ፍጆታ ይውል ዘንድ የጥቃቅን እና አነስተኛ አባላትን ተጠቃሚነት በማሰብ አዘጋጅ ክፍሉ 4,000 እንጀራ እንዲጋግሩለት ቀብድ ከከፈለ በኋላ አቶ ብርሀኑ የተሰኙ የቀበሌ ሊቀመንበር ባሳደሩት ጫና ምክንያት ዱቄታችሁን ውሰዱ መባሉ ወሬው ተዳርሶ ሲያበቃ ፕሮግራሙ መድረክ ላይ ባለበት ሰዓት እንኳን ከክርስትያኑ ህብረተሰብ ሳይቀር በነፍስ ወከፍ እየቀረበ ያለው የእንጀራ መጠን ከ 70,000 በላይ መዝለቁ የተበሰረበት ይገኛል፡፡ከዚህ ጋር ተያይዞ ታዳሚውን ማስጠለል ያስችል ዘንድ ድንኳን ባስፈለገበት ሰዓት የገብርኤል ቤተክርስትያን እና መካነ እየሱስ ያደረጉት አስተዋጽኦ ተወድሷል፡፡
ሰፊ ሰዓት ወስዶ ከቀደምት የሙስሊሞች ታሪክ በመነሣት አሁን ያለውን ተጨባጭ ለመዳሰስ የሞከረው አህመዲን ጀበል ታሪክን ጠንቅቆ እንደሚያውቅ እና ሙስሊሙም ታሪኩን ጠንቅቆ በማወቅ አንድነቱን ማስጠበቅና የታሪክ ጉዳፋ በመፍጠር ሙስሊሙን በማታለል ለህዝበ ሙስሊሙ ሳይሆን ለራሳቸው ጥቅም በመሯሯጥ ላይ ከሚገኙት አካላት ራሱን እንዲጠብቅ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡ አህባሽን በተመለከተ ህዝቡ ከብዥታ የጠራ አመለካከት እንዲኖረው በማስቻል ጠቃሚ መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን አህባሽ ሱፍያ ነኝ የሚለው ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌለው ተጨባጭ ምሳሌዎችን በማጣቀስ አጋልጧል፡፡ ሱፊያዎች ፈፅሞ ሰው እንደማያከፍሩ የተናገረው አህመዲን አህባሾች ሱፊያዎች ነን እያሉ እንኳን በዓለም ላይ ታዋቂ የሆኑ የሱፍያ ዑለሞችን ሣይቀር ማክፈራቸውን ተጨባጭ መረጃዎችን በማቅረብ አስረድቷል፡፡
አሁን በቦታው ላይ የተቀመጡት የመጅሊሱ አመራሮች ህዝብ ያልመረጣቸው ከመሆኑ በተጨማሪ መጅሊስ ምርጫ ካካሄደ አስራ ሁለት ዓመታት አስቆጥሯል ያለው አሕመዲን ከህዝብ እውቅና እና ፈቃድ ውጭ መተዳደሪያ ደንቡን እንደፈለጉ እየቀያየሩት ዛሬም እንደትላንቱ ሙስሊሙን ለመበደል ቆርጠው ስለተነሱ በቃችሁ ልንላቸው ይገባል በማለት ህዝቡ በተያያዘው ሰላማዊ የመብት ጥያቄ ላይ እንዲገፋበት አሳስቧል፡፡
የዙህር ሰላት መሰገድን ተከትሎ የፕሮግራሙ ዋና አካል የነበረው የሶደቃ ስርዓት የተካሄደ ሲሆን ቁጥሩ እጅግ ከፍተኛ የነበረው ታዳሚ በጣም ባማረ ስርዓት የቀረበለትን ማዕድ ተቋድሷል፡፡
ከምሳ በኋላ ፕሮግራሙ በመቀጠል አዝናኙ የደረሳው ሠይድ ዝግጅት የቀረበ ሲሆን በአፍሪካ ቴሌቪዥን ብቻ የሚያውቁት በአካል የማየት እድሉን በማግኘታቸው በደስታ ስሜት ተከታትለዋል፡፡ ምንም እንኳን ምንጩ ወሎ ቢሆንም ደረሳው ሰይድ በወሎዬዎች መካከል ሆኖ ያቀረበው የመድረክ ዝግጅት በሳቅና በተክቢራ ታጅቦ ለመድረኩ ድምቀት ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡
ከዚህ በመቀጠል በአንፃሩ ሰፊ ሰዓት የመድረክ ቆይታ የነበረው የካሚል ሸምሱ ንግግር ሲሆን በእጁ የያዛቸው “አዲስ ራዕይ” የተሰኘ የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ. መፅሔትና የህገ-መንግስቱ መፅሀፍ ለንግግሩ መነሻና መድረሻ ሀሳቦች ማጣቀሻዎች ነበሩ፡፡ ካሚል በንግግሩ አጽንኦት በሰጣቸው ነጥቦች መንግስት በሐይማኖተ ጣልቃ መግባቱን እና ምርጫን አስመልክቶ እየተደረገ ያለው ነገር ኢ-ሕገመንግስታዊና ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በመሞገት ለህዝብ በማስረዳት መብትን በማስከበር ሂደት ማንም ምንንም መፍራት እንደሌለበት የአብሽሩ መልዕክቱን አድርሷል፡፡
ከነበረው የሰዓት መጣበብ የተነሳ መድረክ ላይ በመቅረብ መልዕክት ማስተላለፍ የሚገባቸው ታዋቂ ግለሰቦች መልዕክት ሳያሥተላልፉ ቢቀሩም የቄራ መስጂድ ምክትል ኢማም ሰዒድ ዓሊ (አጭር መልዕክት ካስተላለፈ በኋላ በቀረበለት ጥያቄ መሠረት በጣፋጭ አንደበቱ አላህ ካገራለት ጥቂት የቁርኣን አንቀፆች አሰምቷል)፣ ኡስታዝ ዓብደዱል መናን፣ ሸኽ ኢድሪስ ደጋን እድሉን ካገኙት ይገኙበታል፡፡
የፕሮግራሙ ታዳሚዎች ፕሮግራሙ መቀጠል እንዳለበት በተክቢራ እና በንግግር ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩ አግራሞትን የፈጠረ ሲሆን የፕሮግራሙ መቋጨት ግድ ሆነና የመጣው እንጀራ ባለማለቁ ምክንያት ራት መብላት የሚፈልግ መብላት እንደሚችል መልዕክት በማስተላለፍ እንዲሁም ለፕሮግራሙ መሳካት የበኩላቸውን ሚና ለተጫወቱ ሁሉ ምስጋና በማቅረብ የመድረኩ መሪዎች ፕሮግራሙ መጠናቀቁን በማብሰር 11፡35 ላይ የመድረኩ ውሎ ተቋጭቷል፡፡

ድምፃችን ይሰማ!

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on April 13, 2013 in Uncategorized

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: