RSS

ባቲ የአንድነትና የሰደቃ ዝግጅት ተካሄደ! (እሁድ ሰኔ 17 2004)

13 Apr

ባቲ የአንድነትና የሰደቃ ዝግጅት ተካሄደ!
(እሁድ ሰኔ 17 2004)

ኧረ ባቲ ባቲ ባቲ ገንደ ድዩ
ደምቆ የዋለውን ሀድራችንን እዩ

ብለን የዛሬውን የድምፃችን ይሰማ የባቲና አካባቢዋ ሙስሊም ኅብረተሰብ የአንድነትና የሶደቃ ፕሮግራም ዘገባ እነሆ ብለናል፡፡
ከፍተኛ የወንዶችና ሴቶች ቁጥር እንደታደመበት የተስተዋለው እና በባቲ የተካሄደው ደማቅ የአንድነትና የሰደቃ ፕሮግራም በሠላም ተጠናቀቀ፡፡ ፕሮግራሙ እንዳይካሄድ እና ህዝቡም በዝግጅቱ ላይ እንዳይሳተፍ ለመንግስት ሰራተኞች ሳይቀር ትእዛዝ ቢተላለፍም ይህንን ችላ በማለት ወደ ዝግጅቱ መትመም የጀመረው ገና በጧቱ ነበር፡፡ ህዝቡን ወደ ዝግጅቱ በማምጣት የከተማዋ ባጃጆች፣ሚኒባሶችና እና ቅጥቅጥ አውቶብሶች “ለታላቁ አንድነት እና የሶደቃ ፕግራም ነፃ አገልግሎት” የሚል ባነር በመለጠፍ አገልግሎት ሲሰጡ ተስተውሏል፡፡ የተጠናከረ የፍተሻ ስርዓቱ የተሳለጠ መሆኑ ምንም ዓይነት አደናቃፊ ነገር ሊከሰት እንደማይችል አመላካች የነበረ ሲሆን የመድረክ ማስዋብ ዝግጅቱን ጨምሮ የአዳራሽ (የዳስ) ዝግጅትና ሌሎችም ተገቢውን ወቅት ጠብቀው የታዳሚውን መምጣት ብቻ በመጠባበቅ ላይ ነበሩ፡፡ ከባቲና በዙሪያዋ ከሚገኙት ከተማዎች ከተገኙት ታላላቅ ኡለማዎችና ሙስሊም ህዝብ በተጨማሪ ዶ/ር ሐጅ ኢብራሒም፣ የቄራ መስጂድ(አዲስ አበባ) ኢማም ሸኽ ሠይድ፣ ዶ/ር ዓብደላህ ኸድር፣ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል፣ ሸኽ መከተ ሙሔ፣ ኡስታዝ ሐሰን ታጁ፣ ወጣት ሪድዋን፣ ኡስታዝ በድሩ ሁሴን፣ ኡስታዝ ፈይሰሉዲን፣ የመንዙማው ሰው ራያ አባ ሜጫ እንዲሁም የሙስሊሞች ጉዳዮቹ አክመል፣ ኢስሐቅ እና ዩሱፍ ጌታቸው ከአዲስ አበባ በእንግድነት ከተገኙ ታዳሚዎች ከፊሎቹ ነበሩ፡፡
የመድረክ መሪውን አረቢኛ የመድረክ መክፈቻን ተከትሎ የቀረበው የባቲ ከተማና አካባቢዋ ታላላቅ የአገር ሽማግሌዎች ዱዓ 3፡30 ላይ መደረጉ የዕለቱን ፕሮግራም መጀመር አበሰረ፡፡
“በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ኢስላም ያሳለፈው ችግር፣ አሁን ያለበት ተጨባጭና የወደፊቱ ቀጣይ ሁኔታ” በሚል ርዕስ መድረክ ላይ የተሰየሙት የመጀመሪያዎቹ የመድረኩ ሰዎች ኡስታዝ ሐሰን ታጁ እና ኡስታዝ በድሩ ሁሴን ነበሩ፡፡ እንዲህ እንድንሰባሰብ ላደረገን አሕባሽና አሕባሽን ላመጡልን ምስጋናችን ይድረሳቸው በማለት ንግግሩን የከፈተው የመጀመሪያው ተናጋሪ ኡስታዝ ሐሰን ኢስላምና ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የሳለፉትን የመከራና የግፍ ታሪክ መረጃዎችን በማጣቀስ ያስረዳ ሲሆን ቀደምት መንግስታት ሙስሊሙን እንዴት እንከፋፍለዋለን፣ እንዴት እናከፍረዋለን እንዲሁም ኢትዮጵያን እንዴት ክርስትያን እናደርጋታለን የሚሉ እስትራቴጂዎችን ይጠቀሙ እንደነበር እያንዳንዱን እስትራቴጂ ከተግባራዊ ምሳሌዎች ጋር በማጣመር የነበረውን እውነታ አሳይቷል፡፡ ይህ ሁኔታ (ስትራቴጂ) አሁን ባለው ትውልድ ላይ እንደማይሰራ የተረዱት የአሁኑዎቹ ደግሞ ገንዘባቸውን ከመጠቀም ጀምሮ ዘዴ በተሞላበት ሁኔታ ሙስሊሞችን መከፋፈልና ሙስሊሙ እንዲህ ሊደርግህ ነው በማለት የሌሎች እምነት ተከታዮችን በማነሳሳት ጥላቻን መፍጠር ብሎም ወደ ግጭት እንዲያመራ ማድረግ የሚሉትን ሁለት ዋና ዋና ስትራቴጂዎች በመጠቀም ላይ ይገኛሉ በማለት ዘመነኛውን ዘዴ ከቀደምት አገዛዝ የጭቆና ዘዴ በማነፃፀር አቅርቦታል፡፡ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር ያለንን የወንድማማዊነት ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እና በመካከላችን ያለውን ግንኙነት ማጠናከር የሚሉት ሁለት ነጥቦች ኡስታዝ ሐሰን ከፊታችን ለተደቀኑበት የተንኮል ውጥኖች እንደ መፍትሄ ያቀረባቸው ሀሳቦች ነበሩ፡፡
ኡስታዝ በድሩ ሑሴን ኢስላም አሁን ያለበት ሁኔታ የጨለመ ቢሆንም መጪው ግን ብሩህ ነው በማለት ሰፊ ጊዜ በመውሰድ ልብ የገዛ ንግግሩን አሰምቷል፡፡ ሁስታዝ ሐሰን ጠቆም አድርጎ ያለፋቸውን ሁለት የመፍትሔ ሐሳቦች በመንተራስ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ያቀረበው ኡስታዝ በድሩ ሙስሊሙ ህዝብ ከዚህ አንጻር ሊፈጽማቸው ይገባል ካላቸው ዋና ዋና ነገሮች መካከል ለውጭ ኃይላት ፈጽሞ አለመንበርከክ፣ የውስጥ አንድነታችንን ይበልጥ ማከም ፣ የዳዕዋ ትምህርቶችን ማስተካከል እንዲሁም ወደ ዓሊሞቻችን መመለስ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ አደራችን አንድነት ነው፣ አደራችን ፍቅር ነው፣ አደራችን መቻቻል ነው በማለት በከፍተኛ የተክቢራ አጀብ መሳጭ መልዕክቱን ያስተላለፈው ኡስታዝ በድሩ የንግግሩን መቋጫም በዚሁ በማድረግ መድረኩን ተሰናብቷል፡፡
ረያ አባሜጫና ወንድም ሙሐመድ ጀማል (የዕለቱ የመድረክ መሪ) ጣዕም ያላቸውን አነቃቂ ነሺዳዎች በየተራ በማቅረብ ህዝቡን ዘና ማድረግ ችለዋል፡፡
ቀሪውን እና እስከ ዙህር ሦላት ድረስ የነበረውን የመድረክ ቆይታ ያደረጉት የሙስሊሞች ጉዳይ መፅሔት ባልደረቦች አክመል ነጋሽና ኢስኃቅ እሸቱ ነበሩ፡፡ ሁለቱ ተናጋሪዎች በመተጋገዝ በነበራቸው ቆይታ ወቅታዊውን የሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ከመነሻው አሁን እስከደረሰበት ደረጃ ያለውን ተጨባጭ በሰፊው አስረድተዋል፡፡ የሙስሊሞች ጥያቄ ፍፁም ሠላማዊ፣ ህጋዊ እና ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን የጠበቀ መሆኑን ከነባራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች በመነሳት ያስረገጡ ሲሆን አቅጣጫውን ያልተገባ ስዕል በመስጠት አቅጣጫውን ለማስቀየር የሚደረጉትን ከንቱ ሙከራዎች ለህዝቡ ይፋ አድርገዋል፡፡ ጥያቄው ፖለቲካዊ ነው፣ ጥያቄው ሸሪዓዊ መንግስት የማቋቋም ጥያቄ ነው፣ ሕገ-መንግስቱን ያወግዛሉ፣ ተቃውሞው ሠላማዊ አይደለም፣ ተቃውሞውን እያነሱ ያሉቱ የነባሩ እስልምና አባል ያልሆኑ ናቸው፣ መቻቻልን የሚያደፈርሱ ናቸው፣ ካራቴ ይማራሉ የሚሉት የመብት ጥያቄዎቹን አቅጣጫ በማሳት የሚፈልጉትን እርምጃ መውሰድ እንዲያስችላቸው የሚያቀርቧቸውና እያቀረቧቸው ያሉ መሠረት የሌላቸው ወሬዎች ናቸው በማለት ሙስሊሙ ህዝብ ጥያቄዎቹ ምላሽ እንዳላገኙ በማመን እየሄደበት ያለውን ሠላማዊ ሂደት አጠናክሮ እንዲቀጥል በማሳሰብ የሁለቱም የመድረክ ውሏቸው ተጠናቆ የዙህር ሶላት እና የምሳ መብላት ስርዓት ቀጥሏል፡፡
የከሰዓት የዝግጅቱ ውሎ በረዳት ፕፌሰር አደም ካሚል የተጀመረ ሲሆን ከወሎ ኢስላማዊ ታሪክ ጋር በተያያዘ ሰፋ ያለ ጊዜ በመውሰድ ወሎ የኢስላም ባለውለታ መሆኗን አስረድቷል፡፡ ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ አህባሽ ለህዝብ፣ለአገርና ለመንግስት የማይበጅ መሆኑን እና እስልንናን ማስተማር ተፈልጎ ከሆነ አገራችን እስልምናን የምታውቀው ከአረቦች ከራሳቸው በስተፊት በመሆኑ ከሊባኖስ ለሚመጡት ይቅርና ሊባኖስ ውስጥ ላሉት ሸኾቻቸው ብሎም ለዓለም ሙስሊም የሚተርፉ አንቱ የተሠኙ ታላላቅ ዓሊሞች ባለቤት በመሆናችን ይህ ሂደት ሊስተካከል እንደሚገባ በአፅንኦት ተናግሯዋል፡፡ አህባሽ ሊባኖስ ውስጥ የሚታወቀው የብጥብጥ መርዙን በመርጨት በመሆኑ ይህንን መርዙን አገራችን ውስጥ እንዲረጭ ፈጽሞ የማንፈቅድለት በመሆኑ መንግስት ሁኔታውን በድጋሜ ሊያጤነው እንደሚገባ በማሳሰብ ንግግሩን ቋጭቷል፡፡
ሰሞኑን በወሎ ምድር ቆይታ ያደረገው ደረሳው ሰይድ ዛሬም ታዳሚውን በማዝናናት እና በማሳቅ ቁም ነገር አዘል መልዕክቱን ለተመልካቹ አድርሷል፡፡
ከዶ/ር ዓብደላ አጠር ያለ የመድረክ ቆይታ በኋላ “አሕባሽን ለምን እንቃወማለን” በሚል ርዕስ ቀጣዩን የመድረክ ቆይታ ያደረገው ሰው ዳዒ ፈይሰሉዲን ነበር፡፡ አሕባሽ ኢትዮጵያና ሌሎች የዓለም ክፍሎች ላይ ያለው ዓላማ ዲኑን የማስተማር ሳይሆን የሚከተሉትን አራት አላማዎች ዳር ማድረስ እንደሆነ በመግለፅ እንደሚከተለው ዘርዝሯቸዋል፡፡ 1ኛ. ሕዝበ ሙስሊሙን መከፋፈል 2ኛ. ህዝበ ሙስሊሙን ያለ መሪ እና ታማኝ መፅሐፍት (ኪታቦች) ማስቀረት 3ኛ. የሙስሊሙን ሥነ-ምግባር ማበላሸት እና 4ኛ. ኢስላምንና ሙስሊሙን ለማስመታት ለኢስላም ጠላቶች በር መክፈት የሚሉት ናቸው፡፡ አህበሾች እነኚህን አራት ዓላማዎች ለማፈፀም የሚከተሉትን አምስት ዘዴዎች ይጠቀማሉ ብለዋል፡፡ እነሱም፡- 1ኛ. እነሱ (አህባሾች) የሚሉትን የማይቀበሉ ዑለሞችን ማክፈር 2ኛ. ውሸትን መናገር እና መፃፍ 3ኛ. “ሻዝ” ወይም ጥራዝ ነጠቅ የሆኑ ፈታዋዎችን ማሰራጨት 4ኛ. የኺላፍ ነጥቦችን አግዝፈው በማቅረብ ጭቅጭቅ መፍጠር እና 5ኛ. ለኢስላም ጠላቶች ፍቅር ሲኖራቸው ሙስሊሞችን ደግሞ መጥላት የሚሉት ናቸው በማለት ለእያንዳንዱ የማስፈፀሚያ ዘዴዎቻቸው ከዚህ ቀደም ያደረጓቸውን በተጨባጭ ምሳሌ በማስደገፍ ሙስሊሙ ህዝብ እንደ ከዚህ ቀደሙ አሁንም ጠንካራ የአንድነት ክንዱን በማስተባበር አሕባሽን መታገል እንደሚኖርበት የጠነከረ አደራቸውን አስቀምጠዋል፡፡
ፕሮግራሙ በከፍተኛ ሞቅታ እንደዘለቀ መገባደጃው ላይ ሲደርስ የመዝጊያውን የዱዓ ሥርዓት ዶ/ር ሀጅ ኢብራሂምና የቄራ መስጂድኢማም ሸኽ ሠይድ ዱዓ በማድረግ የዕለቱ ታላቁ የአንድነትና የሶደቃ ዝግጅት የሚጠበቅበትን ዓላማ በሚገባ አሳክቶ እንግዶቹን በጊዜ ወደየመጡበት ሸኝቷል፡፡

አላህ ይቀበላቸው!

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on April 13, 2013 in Uncategorized

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: