RSS

የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ጉዞና የሰላማዊ ትግሉ ሁነቶች

07 Apr

                 የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው ጉዞና የሰላማዊ ትግሉ ሁነቶች    (ግላዊ ዕይታ)

                                       ከጥር -ግንቦት, 2004

ቢን ሙሀመድ፡  ግንቦት 29፡ 2004
by Bin Moh (Notes) on Thursday, June 7, 2012 at 11:06am
መግቢያ 

በአላህ ስም እጅግ በጣም አዛኝ በጣም ርህሩህ  በሆነው፡-

ከወራት በፊት በአወሊያ የተፈጠረውን የአህባሽና የመጅሊስ ተቃውሞን ተከትሎ ህዝበ-ሙስሊሙ የሚያምንባቸውንና ጥያቄዬን ለመንግስት ያቀርቡልኛል፣ መፍትሄ ያፈላልጉልኛል ያላቸውን ከመካከሉ መረጦ ህጋዊነትን በተላበሰ መልኩ እንዲጓዙ ትልቅ ኃላፊነት በማሸከም “የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ” ብሎ መሰየሙ ይታወሳል፡፡

በዚህ ፅሁፍም ውስጥ ጸሃፊው የኮሚቴውን ውልደት፣ መዋቅርና ስልታዊ ጉዞ፣ ስኬትና ጥንካሬዎች፣ እንዲሁም ስጋትና ተግዳሮቶችን ለህዝበ-ሙስሊሙ በግልጽ በማቅረብ ግላዊ ሀተታውን ያሳያል፡፡

የዚህ ፅሁፍ ዋነኛ ዓላማ ግን በመንግስት በኩል እየጠነከረ የመጣውን እና ኮሚቴውን ከህዝበ-ሙስሊሙ የመገንጠል፣ ለይቶ የመምታትና የሰላማዊ መብት ጥያቄ ሂደቱን ለማኮላሸት የሚደረገውን ሴራ ለሙስሊሙ በማስረዳት፣ ቅድመ-ጥንቃቄ ለመጠቆም፣ የኮሚቴውን አካሄድ ግንዛቤ ለመስጠትና ሀገራዊ የትግሉ ሁነቶችን ለማመላከት ብሎም የሚካሄዱትን ሴራዎች በጋራ እንድንዋጋ፣ አንድነታችችንን በበለጠ እንድናጠናክር የሚደረግ ጥሪ ነው፡፡

ይህ ፅሁፍ የጸሃፊው ትዝብት፣ እምነት፣ ጥንቅርና ትንተና እንጂ የኮሚቴው አቋምም ሆነ ፅሁፍ አለመሆኑ እንዲታወቅ ፀሃፊው በአፅንኦት ያሳስባል፡፡

ተቃውሞን ከስላቅ

በመጅሊሱ የሰላምና ጸጥታ ሃላፊ አቶ ጀማል ተፈርሞ ታህሳስ 21/2004 አወሊያ ግቢ የደረሰው ደብዳቤ 50 የአረብኛ መምህራንን በማሰናበት ኮሌጁን ሲዘጋ፣ የ20 ዓመት አገልጋይ ኢማም ሐጅ ዑመርንም ከነምክትላቸው ከስራ አገደ፡፡1 ይህ ውሳኔ ያስቆጣቸው የኮሌጁና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች ታህሳስ 24 ቀን “ኢማሙና መምህራኖች ይመለሱልን፣ ኮሌጁ ይከፈት!” በማለት የተቀውሞ ድምጽ ማሰማት ጀመሩ፣ በሁለተኛው ቀን አቶ ጀማል ወደ አወሊያ ጎራ በማለት በስላቅና በፌዝ “የተባረሩት በስህተት ነውና ነገ ይመለሳሉ” ቢልም ተፈፃሚ ሳይሆን ከሳምንት በላይ ዘለቀ፤ ማክሰኞ ጥር 1 ቀን የመጅሊሱ ዋና ጸሓፊ አል-ሙሀመድ ሲራጅ መጥቶ ሌላ ስላቅ ሲጨምርበት ተቃውሞው ወደ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋገረ-“የመጅሊስ አመራሮች ይውረዱ!” “አሸዕብ..ዩሪድ..ኢስቃጠል..መጅሊስ!” በሚል ህብረ-ዜማ ታጅቦ፡፡ ተቃውሞውንም ወደ 24 ሰዓት ሲያሳድጉት መጅሊሶች በመደናገጥ ጫና ቢፈጥሩም ተማሪዎቹ “ጁሙዓ አወሊያ እንገናኝ!” ግብዣቸውን አጧጧፉት፣ በዚህም አርባ ሺህ የሚገመቱ ምዕመናን አወሊያ ሰገዱ-ጥር 4፡፡ ለሳምንትም ቀጠሮ ያዙ፤ ተማሪዎቹ ለመቀጠል ቢሞክሩም ቅዳሜ ረፋዱ ላይ ግን መጅሊስ ከግቢው አስወጣቸው፡፡ ተማሪዎቹ ከግቢው መልቀቃቸው ንዴት የፈጠረባቸው ሌሎች ግለሰቦች እሁድ ዕለት ዳግም ግቢውን በመሙላት  በቁጣ “መጅሊስ መውረድ አለበት!” ሲሉ ተወያዩ፡፡ ለቀጣዩ አርብም ቀጠሮ ያዙ፡፡2

የኮሚቴው ውልደት

በጥር 11 ዓርብ 60ሺህ በሚገመቱ ሙስሊሞች ትዕይንተ-ህዝብ ሲካሄድ ጥያቄውም ከተማሪ አጀንዳነት ወደ ህዝብ አጀንዳነት በይፋ ተላለፈ፡፡ 20 አባላት ያሉት በዳዒያንና ወጣቶች ብቻ የተሞላ ኮሚቴ ተዋቀረ፣ ኮሚቴው የተቃውሞ ፊርማ ማሰባሰቡን ተያያዘው፣ የህዝቡን ስፍር የለሽ በደሎችና ጥያቄዎች ወደ ሰባት በመጭመቅ ለመንግስት ለማቅረብ ሲንቀሳቀስ ባለሙያዎችን ሲያማክር የውክልና ሂደቱ ትክክለኛ ቅርጽ አለመያዙን በመረዳትና ስብጥራቸውን በመመርመር ማሰተካከል እንደሚገባቸው በመስማማት በቀጣዩ ዓርብ ጥር 18 ፊርማውና ስብጥሩ በአዲስ መልክ እንዲካሄድ ለህዝብ አቀረቡ፤ በዚህም ከዳዒያን፡ ወጣቶች፣ አባቶች፣ ምሁራን፣ ነጋዴዎችን ያቀፈ 17 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተዋቅሮ በአንድ ቀን ብቻ ከ60ሺህ በላይ ፊርማ የተሰበሰበ ሲሆን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ከ500ሺህ በላይ የውክልና ፊርማ ሲረከቡ፣ ከየክልሎችና ከተሞች፣ እንዲሁም ከውጭ ሀገር ከሚኖሩ ሙስሊም ኢትዮጲያውያን ከሚላኩ የድጋፍና ውክልና ደብዳቤዎችና የአቋም መግለጫዎች፣ ብሎም በወኪል መልዕክተኞች አማካኝነት አጠቃላይ ከሀገሪቱ ሕዝብ ብዛት ውስጥ ወደ 45.8% 3 የሚገመቱ ኢትዮጲያውያን ሙስሊሞች “ጥያቄያችንን ለመንግስት አድርሱልን” ብሎ ሃላፊነት ሰጣቸው፡፡4

 ጉዞ ምዕራፍ፡ አንድ…..እስከ የካቲት 26 

ይህን የመጀመሪያውን ጉዞ ብዙዎች “ተስፈኛው ምዕራፍ” (optimistic period) ይሉታል፡፡ለዚህም መንግስት የመብት ጥያቄውን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚመልሰው ያላቸውን ሙሉ እምነት በማስታወስ፡፡ ኮሚቴውም ኃላፊነትን ተረክቦ ራሱን በማዋቀር ሰብሳቢ(አሚር)-ዑስታዝ አቡበክር አህመድን፣ ምክትል ዑስታዝ አህመድ ሙስጠፋን፣ የህዝብ ግንኙነት-ዑስታዝ አህመዲን ጀበልን እና ሌሎችንም ሰይሞ በጉዳዩ ላይ በጥልቀት በመወያየት፣ ባለሙያዎችን በማማከር፣ ልምዶችን በመቅሰምና የችግሮቹን አንኳር መንስኤ ነቅሶ በማጥናት ጥያቄዎቹን ይበልጥ ወደ ሶስት(3) በመጭመቅ ሲያስቀምጥ በቀዳሚነት “አሁን ያሉት የመጅሊስ አመራሮች ተነስተው በህዝብ በሚመረጡ አዳዲስ አመራሮች ይተኩ”፣ “የአህባሽ አስተምህሮ በግዳጅ አይጫንብን” እና “አወሊያና ሌሎች ተቋሞች በሙስሊሙ በተመረጡ ይመሩ” የሚሉ ሲሆን የሁሉንም ብሶትና ጭቆና በማካተታቸው ከመቼውም በላይ አገር አቀፋዊነትን የተላበሱ አገራዊ መነሳሳትንና አንድነትን የፈጠሩ ሆኑ፡፡ አንደኛው ጥያቄ “መሪ ድርጅታችን ለህዝብ ይመለስ”፣ ሁለተኛና ሶስተኛው ደግሞ “መንግስት እጅህን አንሳልን” የሚሉ አንድምታ አላቸው፡፡

ጥያቄዎቹን በደብዳቤ መልክ ከሰደሩ በኋላ የመንግስት በሮችን ለማንኳኳት አሃዱ ሲሉ አቶ ጁነይዲን ሳዶ በግሉ ቢሮው ይቀጥራቸዋል፣ እነሱም በቀጠሯቸው መሰረት በዕለቱ ቢሮው ሲገኙ  ስብሰባው የእምነት ጉዳዮችን ወደሚመለከተው ፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር መዛወሩን ሲነግራቸው፣ የፌ/ጉ/ሚ በበኩሉ በሚኒስትር-ዴዕታው በኩል ሌላ ቀጠሮ ለየካቲት 10 ይሰጣቸዋል፣ ከዚያም እነደገና ተጨማሪ ቀጠሮ ለየካቲት 26 በመስጠት “ጥያቄያችሁ ገብቶናል፣ መፍትሄ ያገኛል” በማለት ጊዜ ለመግዛት ሞክረዋል፡፡

የሁለት አለም ሰዎች በአንድ ጠረጴዛ–የካቲት 26

ምንም እንኳ ጥሩ ተስፋዎች ቢኖሩም መጅሊስ የሚሰራውን ፀያፍ ድርጊቶች መቀጠሉንና ተቆጭ ማጣቱን፣ ብሎም የአህባሽ አሊሞች በሬዲዮና የመጅሊሱ ፕሬዜዳንት ክብር ተስጥቶት በኢቴቪ (የካቲት 14) መደስኮሩን ተከትሎ የጥያቄውን መልስ ተስፋ ሊያጨልመው ችሏል፡፡ ቀኑም ደረሰና ከጧት መጅሊሶች ከሰዓት ኮሚቴው በአንድ ጠረጴዛ ተሰየሙ..ከሰብሰባ መሪዎች ፖለቲካ የሚተነፍጉ ቃላቶች ሲረጩ ከመድረክ ደግሞ ኢስላማዊ ቃላቶች…አልተገናኝቶ! የሁለት አለም ሰዎች ይሉሃል ይህ ነው፡፡ ስብሰባ መሪዎቹ በፍረጃ ወዲያው ሊቋጩት ቢሞክሩም ወደ 6 ሰዓት የፈጀ የጦፈ ክርክር አደገ ነገር ግን ስብሰባው ሳይቋጭ በእረፍቷ ሰዓት ውስጥ ያንኑ ህቡዕ ውሳኔያቸውን በአንድ “የግል” ራድዮ ጣቢያ ንፋስ ለቀቁ፡፡

ጉዞ ምዕራፍ፡ ሁለት…..እስከ ሚያዚያ 19

ከየካቲት 26 በኋላ ነበር ኮሚቴው ሁሉ ነገር የገባው፣ ትልቅ ቁጣን አስከተለ፣ ተቃውሞው ይበልጥ ጦፈ፣ ኮሚቴውም መልሶቹን እንደማይቀበል በደብዳቤ ለፌደራል ጉዳዮች ካሳወቀ በኋላ ባለ7 ገጽ ደብዳቤ የጠ/ሚንስትሩን ቢሮ ጨምሮ ለ10 የመንግስት መ/ቤቶች አስገባ፣ ጠ/ሚሩንም በአካል ለማናግር ቢሞክር…ጸጥ….መልስ የለም፡፡6 የተቃውሞን መጠንከርና ወደ ሌሎች መሳጂድና ክልሎች መዛመቱን የተረዳው መንግስት የተቻለውን ሁሉ ጉዳዮን ለማጠልሸት ሞከረ፡፡ ኮሚቴውም የአንድ ወር እረፍት በመስጠትና ሰላማዊነቱን በማሳየት ሲሞክር፣ የመንግስትን ባህሪ በጥልቀት ከሚያውቁ ሰዎች ነገሮችን ሲረዳ፣ የጠ/ሚኒስትሩም ሚያዚያ 5 ቀን በፓርላማ ብቅ ብለው ከማሳቅ ይልቅ ማሳቀቅ በበዛበት ውሏቸው የፍረጃ አቋማቸውን ሲያውቅ፣ ይህም ይባስ ቁጣን ጨምሮበት ቀጠሮው ደርሶ የ1966ቱን ታሪካዊ ድግግሞሽ ትዕይንተ-ህዝብንም ለማስታወስ ሚያዚያ12 ወደ አንድ ሚሊዮን (በሀገሪቷ ታሪክ ትልቁ) የሚገመት ምዕመናን በአወልያ ተገኝቶ ሰላማዊ ተቃውሞውን አሰማ፣ ይህም አለምን በማስደመሙ ለህዝብ እይታ በአልጀዚራ በኩል ለመጀመሪያ ጊዜ ለአለም ብቅ አለ፡፡ ኮሚቴው አሁንም ሌላ ቀጠሮ በመስጠት ባለ22 ገጽ “የሀሰት ፐሮፓጋንዳ መደጋገም የእምነት መብት ጥያቄን ህገ ወጥ አያደርውም” በሚል የአቋም ደብዳቤ ጉዳዩን ይበልጥ ለማብራራት ሞክሯል፡፡7 ተቃውሞውም በአንዋርና በኑር መስጅዶች ቀጠሎ ሳለ ሚያዚያ 19 የአሳሳ ንጹኃን ምዕመን በፖሊሶች መገደልን ተከትሎ ሌላ ትልቅ ቁጣ አስከተለ፡፡

ጉዞ ምዕራፍ፡ ሶስት…..እስከ…

አካሄዱ ያላማረውና የመንግንስትን የወደፊት የጥፋት እቅዶች7 የተረዳው ኮሚቴው ከተክቢራ ሌላ የዝምታ ተቃውሞን ለሀገሪቱ በማሰትዋወቅ ሙቀቱን ለማብረድና ሰላማዊነቱን በድጋሜ በማሳየት ሴራዎችን ለማክሸፍ ሰርቷል፡፡ በዚህም አካሄድ ለሚሰነዘሩ ውንጀላዎች አፀፋዊ መግለጫ በማውጣትም ማስተባበሉን አበክሮ የሰራበት ሲሆን፤ ለአካሄዱ መረጃን መሰረት በማድረጉ የተዋጣለት ጉዞ መሄድ ችሏል፤ ይህም አካሄዱና ህግን መሰረት ማደረጉ ሰላማዊና ለሰላም መቆሙን ከማመልከቱም አልፎ የመንግስትን ክስ ያዜሮዋል(vanish)፡፡ ይህ የሚያሳየው የኮሚቴውን ብስለትና የንቃት ደረጃ ከፍታ ሲሆን መንግስት ኮሚቴውን ከህዝቡ ለመገንጠልና ለይቶ ለመምታት ያመቸው ዘንድ የሚደረገውን ያለ ግልፅ ማስረጃ መግለጫ  እንዲሰጥ ጉትጎታዎችንና የማሳሳት ዘመቻዎችን ከግምት ውስጥ እንድናስገባ ስለመረጃ ሃይልነት በተግባር ከማሳየትም አልፎ ሁላችንም የድርሻችንን መረጃዎችን በማጠናቀር እንድናገዘው መረጃ ለማገኘት እንዴት እንደተቸገረ በመግለጽ በማስረዳት አካሄዱን መስመር ማሰያዝ ችሏል፡፡

ተግዳሮቶች (challenges)

1.ፍረጃና ማጠልሸት፡ መጅሊሱ “አል-ቁድስ” ጋዜጣን ጥር ላይ በመግዛት የኮሚቴው አባላትን ስብዕና በማጉደፍ ስራውን አንድ ሲል መንግስት በተራው በሬድዮ ፋና፣ በኢቴቪ፣ በ“ሪፖርተር”፣ “አዲስ ዘመን” እና “ሰንደቅ” ጋዜጦች በመጠቀም የዶ/ር አልስተር ስሚዝ አራቱንም የማስቀየሻ ሥልቶች (diversionary tactics)5 በተራም ሆነ በጣምራ መተግበሩን ተያያዘው፡፡ በተለይ “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ “ነፃ አስተያት” አምድ ሶስተኛ ገፅ ላይ እንደሚፅፉ በሚነገርላቸው ቱባ የሃገሪቱ ባለስልጣናት (እንዴ ዊኪሊክስ ሚስጥራዊ መረጃ መሰረት) ያለማንጠልጠያ (ጄኔራል፣ ክቡር፣ ሚኒስትር) በፈጠራ ስማቸው ኮሚቴውንም ሆነ አጠቃላይ ትግሉን “ፀረ-ኢትዮጲያ፣ ፀረ-ልማትና ፀረ-ህገ-መንግስት፣ ፀረ-ሰላም ሃይሎች፣ ፀረ-ዲሞክራሲ፣ ስልጣን ናፋቂዎች፣ አክራሪ፣ አሸባሪ፣ ዋሀብያ፣ ሰለፊያ፣ ድብቅ አላማ ያላቸው፣ ኢስላማዊ መንግስት ናፋቂዎች፣ ፀረ-መቻቻል፣ የውጭ ተላላኪዎች፣ ጥቂቶች፣ በግብር ያኮረፉ፣ የጠረባ ቡድን….”8 እያሉ በመፈረጅ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ወደ ማሸማቀቅ፣ ለሃገሪቷ ስጋትና ምናባዊ ጭራቅ (scapegoat) አድርጎ በመሳል ሌላውን ህብረተሰብ ከጎናቸው ለማሰለፍ ያደረጉት ሙከራ፤

2.ማዋከብና ማስፈራራት፡ የኮሚቴውን አባላት እስከ ሰባት በሚደርሱ የደህንነት መኪኖች የማዋከብና ማስፈራራት፤ የስልክ ንግግሮችን መጥልፍና እንደካሴት ድምጽን መቅረፅ፤ ኢሜሎችን በመፈተሽ10 ፣ስልክ በመደወል ማስፈራራት፣ የግል ኮምፒተሮችን መቀማትና ስብሰባዎችን በማጨናገፍ ሌሎችም የሚድረጉ ውጣ ውረዶች መብዛት(ለህዝቡ መረጋጋት ሲሉ ባይነግሩንም)፤

3.ጥርነፋና ግድያ፡ “ቲ-ሸርት ለብሰሃል፣ ወረቀት በትነሃል፣ አወሊያ ሂደሃል፣ ፊልም አይተሃል/በኮምፒዩተር ጭነሃል፣ ሽብር ነዝተሃል፣ አህባሽን ተቃውመሃል፣ መስጅድ ስግደሃል….(ለሴቶችም ይሰራል)”በማለት እየጨመረ የመጣውና ለጆሮ የሚታክት መታሰር፣ መገረፍ፣ ከስራና ፓርቲ አባልነት መባረር፣ አልፎም አሳዛኝ ግድያዎች (አላህ ለሞቱት የሰማዕታትን ደረጃ ያጎናጽፋቸው) ቁጥር ማሻቀብ ከፈተናም በላይ ትልቅ ስጋት ሆኗል፤

4. ተለዋዋጭ አቋሞች፡ መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ መግባቱን ከመካዱም አልፎ ትላንት በግልጽ “አህባሽዬ” እያሉ ሲያንቆለጳጵሰው የነበረውን ጠ/ሚኒስትሩን ጨምሮ ሽምጥጥ አድርገው መካዳቸውና “ሱፍያ ነው”“ነባሩ እስልምና ነው” ማለታቸው ሌላ ምሽግ መሆኑ፤

5.ጠመቃና መስፋፋቱ፡ የተቃውሞው ውጥረት ቀጥሎ እያለ የአህባሽ ጠመቃ በአዲስ መልኩ መቀጠሉ ለውዝግብ፣ እስራትና ግጭቶች የቅርብ መንስዔ(immediate cause) መሆኑ፤

6. ማግለልና መድሎ፡ ኮሚቴውን “ከነቃህ ይቀራል”በሚመስል መልኩ “አይንህን ላፈር” በማለት መንግስት የውይይት መድረኮችን ሁሉ ዝግ ማደረግ ሰላማዊ ጉዞውን ለመጠምዘዝ ከመጅሊስ ጋር ቅልጥ ያለ ፍቅር ውስጥ መግባቱና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡

ስኬቶች (successes)

1.አንድነት መጠንከር፡ የዳዒያያን ልዩ ተሰጥኦ፣ ችሎታና ልምድ ከግምት ውስጥ ካለማስገባት የተነሳ(እገሌ ሲራ ብቻ፣ እገሌ ተውሂድ ብቻ፣ ተሰውፍ ብቻ፣ ሀዲስ ብቻ፣ ስለአንድነት ብቻ….)እና የኢስላም ጠላቶችን ውንጀላና ፍረጃ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በማስተጋባትና በማራገብ፣ ሁለት ዋነኛ ምክንያቶች የተፈጠሩትን ትናንሽ “ልዩነቶች” በመሰረቱ መፈጥር ያልነበረባቸውን የአህባሽ መምጣት ከስር መሰረቱ ማጥፋቱ፣ ለመከፋፈል የሚደረጉ ሩጫዎችን መልስ ምትና ብሽሽቅ በሚመስል መልኩ በእየመሳጂዱ የሚደረጉ የአንድነትና ሶደቃ ፕሮግራሞች በሀገር አቀፍ ደረጃ መካሄዳቸው፣ በውጭ ሀገራትም እንደዚሁ ትግሉን ለማገዝ ያለልዩነት ታጥቀው መነሳታቸው፤

2.ሀገራዊ መነቃቃት፡ “አህባሽ ማነው ምንድን ነው?” የሚለውን ለመረዳት የሚደረጉ ሩጫዎችና ዳዒያንም ህዝበ-ሙስሊሙን ለመታደግ ሲሉ በሚያደርጓቸው ጥሪዎች ለኢስላማዊ መነቃቃት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱ፤

3.ንቃተ-ህሊና ማደግ፡ ከሁሉም በላይ የኮሚቴው ንቃተ-ህሊና በፍጥነትና ባማረ ሁኔታ ነገሮችን በመረዳት ተንታኞችን በሚያስደምም ሁኔታ የትግሉን አቅጣጫ(በአላህ ፈቃድ) በብቃትና በጥራት በጥቂት ወጭዎች(ጥፋቶች) ማስኬድ መቻሉ፣ ይህም ንቃተ-ህሊና ከሌላው ህብረተሰብ በተሻለ መልኩ በሁሉም ህዝበ-ሙስሊም ላይ በተዋረድ ማደጉ፤

4.የአህባሽ ኑፋቄ ለአለም መጋለጥ፡ የአህባሽ ምናባዊ “አህለ-ሱና ነኝ” ባይነትና ስውር ኑፋቄው ከኢትዮጲያ(ሶስት መጽሃፍትና ሲዲዎች መታተም)አልፎ በአለም ታላላቅ ምሁራን በቴሌቪዥን  ሳይቀር መተቸቱ፣ በድረ-ገፆች እንደልብ መፃፉ ከሙስሊሙ አልፎ አዲስ ለሚሰልሙ ምዕራባውያን ትልቅ ግብዓት ከመሆን በላይ አህባሽን ለመጀመሪያ ጊዜ ትልቅ ውርደት ማከናነቡ፤

5.ከወንበር ወረዱ፡ የመጅሊስ አመራሮች “ከእኛ በላይ ማን አለ” እያሉ ሲጀነኑ በድንገት “ከስልጣናችሁ ውረዱ” መባላቸውና ምርጫ እንዲካሄድ መወሰኑን እንደ ስኬት ሲታይ ይህም ለወደፊቱም ለገንዘብ ብለው ለሚሯሯጥ ድንገት “ውረዱ” መኖሩን እንዲገነዘቡ ማደረጉ፡፡

6.የገጽታ ለውጥ፡ አህባሽ (የሀበሻ ብዙ ቁጥር) የኢትዮጲያውያንን አረባዊ ስያሜ ይዞ በአረቡ አለም በኑፋቄነቱ የፈጠረውን ለሀበሾች ጥሩ ያልሆነ የጅምላ ፍረጃ ገጽታ(image) በዚህ ትግል ሂደት ውስጥ መቀይር መቻላችን እንደ አንድ ስኬት ማየት ይቻላል፡፡

ስጋቶች (risks)

1. አፀፋዊ ስርፀት(backfire bow)፡እንደ ሙስጠፋ አክዮል አባባል “ኢስላማውያን ያለምንም ጭቆና ሲኖሩ የበለጠ ዘመናዊ ሲሆኑ የአስተዳደር ግዴታም ሲጫንባቸው የበለጠ በተግባር (more pragmatic) ይገልፁታል!” በማለት ይገልፃሉ፡፡11 እውነታውም ይህ ሆኖ ሳለ በሀሰት ውንጀላ የሚሰነዘሩ ጭቆናዎች፣ እስራቶች፣ ግርፋቶች፣ ግድያዎችና ስቃዮች ሲበረቱና ከአቅም በላይ ሲሆኑ ሰብዓዊ የመከላከልን ባህሪይ መሰረት በማድረግ አክራሪነት ከሌለበት ምድር እንዳይወለድ ትልቅ ስጋት መኖሩ፤

2.ነጥሎ መምታት፡ መንግስት ካለው ልምድ በመነሳት ኮሚቴውንና የተወሰኑትን ሰዎች ነጥሎ በመምታትና በማሰር የተቃውሞውን ተኩሳት “ማብረድ” በሚል እሳቤ ሊፈፅመውና የባሰ ውጥረት ውስጥ እንዳይገባ ትልቅ ስጋት መኖሩ፤

3.ምርጫና አግላይነቱ፡ የመጅሊሶችን መውረድ ተከትሎ ለምርጫም ሆነ አመራረጥ ስርዓትና ሂደቱ ላይ ሙሉ በሙሉ ኮሚቴውን በማግለል የሚያደርጉት የ”ምርጫ” ሩጫ ከጥቅሙ ጉዳት ስለሚያመዝን ለተጨማሪ ወጥረት መንገድ መጥረጉ፤

4.ለኮሚቴው ልሣን መስጠት፡ ትግሉ የሁሉም ህዝበ-ሙስሊም በመሆኑና ማንኛውም ግለሰብ መረጃ የመስጠትም ሆነ የመቀበል መብት ስላለው በተለያዩ መንገዶች ሁሉም የራሱን ድርሻ እየተወጣ ይገኛል፣ ኮሚቴው ግን የተቋቋመው በአወሊያ ነውና ስብሰባም የሚጠራው ሆነ ሪፖርትና አዳዲስ መረጃዎችንም የሚያቀርበው አውሊያ ግቢ ነው፡፡ ነገር ግን ባለፈው በፌስቡክ “ድምፃችን ይሰማ” ፔጅ የተላለፈውን ዘግናኝ የፊርዶስን ሞት (አላህ የሰማዕታትን ደረጃ ይስጣት) ተከትሎ በኢሳት ሬድዮና ቴሌቪዥን እንደተላለፈው አይነት በኮሚቴው ሰብሳቢዎች በግልፅ ያለተላለፈ መረጃን እነደ ኮሚቴው ልሳን አድርጎ መውሰድ ለኮሚቴው ህልውና እንደስጋት መታየቱ፤

5.ሀገራዊ ቀውስ፡ ከላይ የተጠቀሱት ስጋቶችና ውጥረቶች ተዳምረው ከቀጠሉ ብሶትን በመቀስቀስ ሀገራዊ መልክ ያለው ኢኮኖሚያዊ፤ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስ እንዳያስከትል ያሰጋል፡፡12

መፍትሄዎች (solutions)

የዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ መፍትሄው አጭርና ቀላል ሲሆን መንግስት ህገ-መንግስቱን ከወረቀት ባለፈ ተግባራዊ በማደረግ መጅሊስን ለህዝበ-ሙስሊሙ መልሶ እጁን ከሃይማኖታዊ ድርጅቶች በመሰብሰብ ለዜጎች ተግባራዊ ዴሞክራሲ በማጎናጸፍ፤ 13

ሶስቱን መሰረታዊ የህዝበ-ሙስሊሙን ጥያቄዎች በቅንነት በመመለስም ሆነ ኮሚቴውንና በህዝብ በሚመረጡ አስመራጮችን ያካተተ ግልፅ ትክክለኛ፣ ነጻና ፍትሃዊ የመጅሊስ ምርጫ ማካሄድ፣ አህባሽንም “ወይ በመድራሳህ ወይ ወደ ሊባኖስህ” ብሎ በመፋታት እርቅ ማውረድ፤ 14

ያለአግባብ የታሰሩትንና የታገቱትን በአስቸኳይ በመፍታት፣ የመጅሊስ ጥፋቶችን፣ “ምክራዊ” ውድመቶችንና ድርጅት የማፍረስ ቅጣቶችን በማንሳት በአስቸኳይ ወደ ስራ እንዲገቡና ጤናማ ህይወት እንዲመሩ እድል መስጠት ወሳኝ ነው፡፡

ድል ለኢስላም ነው! አላሁ አክበር!

…………………………………………………………………………………………………………………………………………………………

ENDNOTES

1. “ሠለፊያ” ጋዜጣ፣ ቁጥር 550/1፡ ጥር 4 & 11፡ 2004

2. “የሙስሊሞች ጉዳይ” መፅሄት ቁጥር-17፡ የካቲት 2004 www.yemuslimochguday.net

3.  CIA: The World Fact Book (2007)

4. “የኢትዮጲያ ሙስሊም የት ነው?” መፅሃፍ የካቲት 2004, ገጽ 391-399

5. “የሙስሊሞች ጉዳይ” መፅሄት ቁጥር-18፡ ሚያዚያ 2004

6. “ሰውቱል ኢስላም” ጋዜጣ የካቲት 09፡ 2004

7. ሸህ ጣሃን የመግደል እቅድ፣ ኢሳት ዜና ግንቦት 3፡ 2004 www.ethsat.com

8. “ሰውቱል ኢስላም” ጋዜጣ ሚያዚያ 19/25፡ 2004

9. “አዲስ ዘመን” ጋዜጣ የካቲት 21, መጋቢት 8/9/12/28….,ግንቦት 17፡ 2004 እና ሌሎችም

10. በአ.ኢ.ጋ.ን(SMNE)የተዘጋጀ “አዲሱ ቴሌ” እና “ኢንሳ”፡ የህወሃት/ኢህአዴግ የስለላ ወረብ፡ ሚያዚያ 2004

11. Alemayehu Fentaw, Ethiopia: Are Islamists Coming? TRANSCEND Media Service, May 23, 2012.https://www.transcend.org/tms/?p=19256

12. Jawar Mohammed, Meles’ recycled old tactics being rendered obsolete by a new and shrewd adversary,www.ayyaantuu.com, May 25, 2012.

13. Jawar Mohammed, Growing Muslim Activism and the Ethiopian State: Accommodation or Repression,www.opride.com , March 23, 2013.

14. Alemayehu Fentaw, Is the specter of the Arab Spring haunting Ethiopia? openDemocracy, June 04, 2012.http://www.opendemocracy.net/alemayehu-fentaw/is-specter-of-arab-spring-haunting-ethiopia

 

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on April 7, 2013 in Uncategorized

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: