RSS

‹‹የሃሰት ፕሮፖጋንዳ መደጋገም የእምነት መብት ጥያቄን ህገወጥ አያደርገውም!››

06 Apr

‹‹የሃሰት ፕሮፖጋንዳ መደጋገም የእምነት መብት ጥያቄን ህገወጥ አያደርገውም!››
((ኮሚቴው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ለ10 ሚኒስቴር መ/ቤቶች ያስገባው ደብዳቤ(ሕዝቡ እንዲያውቀው፣እንዲያሳውቀው))

ቀን፡- ሚያዚያ —/2004
ለ————————————
————————————-

ጉዳዩ፡- ህዝበ ሙስሊሙ ያነሳቸውን የመብት ጥያቄዎች ተንተርሶ በአንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት እየታየ ያለውን ህዝብን የማሸማቀቅና የማዋከብ አመለካከትና ተግባርን ለመቃወም የተዘጋጀ የአቋም ማሳወቂያ ፅሁፍ ስለመላክ

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፊት አውራሪነት የተከፈተብንን የእምነት ነፃነት ጥሰት በይፋ መቃወም ከጀመርን እነሆ አራት ወራት አሳለፍን፡፡ በነዚህ ግዚያትም ጥያቄያችንን ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ እያቀረብን ብንገኝም ሊሳካልን የቻለው ያማረ አካሄድ ማስመዝገብ እንጂ ያማረ ውጤትን አይደለም፡፡ ከዚህም አልፎ ጥያቄዎቻችንም ሆነ አቀራረባቸው ምንም አይነት የይዘት ለውጥ ባላመጡበት ተጨባች ሁኔታ በአንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት የሚነዙት የማዋከብና የማሸማቀቅ አመለካከቶችና ተግባራት ህዝበ ሙስሊሙ እነዚህ አቋሞች የመነጩት ከመንግስት ነው ወይንስ መስመራቸውን ካለዩ ባለስልጣናት በሚል አቅጣጫው ባልለየለት መንታ መንገድ ላይ ይገኛል፡፡ በመሆኑም እነዚህንና ሌሎች መሰረታዊ ነጥቦች ላይ ያሉትን ተጨባጭ ሁኔታዎች የሚዳሰስ 22 ገፅ የግንዛቤ ማስጨበጫና የዳግም ጥያቄአችን መልስ ያግኝ አቤቱታ ያካተተ ፅሁፍ ከዚህ ደብዳቤ ጋር አባሪ አድርገን መላካችንን እንገልፃለን፡፡
ከሰላምታ ጋር

ማስታወሻ
ይህ ፅሁፍ በአጠቃላይ ለመላ የሃገራችን ዜጎች በተለይ ደግሞ ለኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሊደርሱ በሚችሉ አማራጭ መንገዶች ሁሉ እንደሚበተን እና እንደሚተላለፍ ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡

የሃሰት ፕሮፖጋንዳ መደጋገም የእምነት መብት ጥያቄን ህገወጥ አያደርገውም!

ህዝበ ሙስሊሙ ያነሳቸውን የመብት ጥያቄዎችን ተንተርሶ በአንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት እየታየ ያለውን ህዝብን የማሸማቀቅና የማዋከብ አመለካከትና ተግባርን ለመቃወም የተዘጋጀ የአቋም ማሳወቂያ ፅሁፍ
ሚያዚያ 2004
አዲስ አበባ

በአላህ ስም እጅግ በጣም ሩህሩህ በጣም አዛኝ በሆነው

I. መግቢያ
ከቅርብ አመታት ወዲህ የሃገሪቱን አንጋፋ ሃይማኖቶች አስመልክቶ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ከሚቀርቡ አሉታዊ ይዘት ካላቸው ዜናዎችና ፕሮግራሞች ውስጥ ‹‹ መቻቻልን የሚያደፈርሱ›› የሚለው ቃል በጋራ ‹‹ነባሩን እስልምና የሚንዱ›› የሚለው ደግሞ ለሙስሊሞች በተናጠል ጥቅም ላይ መዋላቸወ የተለመደ ነው፡፡ በተለይ ለኛ ለሙስሊሞች የቀደምት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ይከተሉት የነበረውን ከምንጩ የተቀዳውን እስልምና ችላ የተባለ በማስመሰል ከኛ በላይ ለኛ የሚያስቡልን መስለው በቀረቡ አካላቶች እየተነገረን ይገኛል፡፡ ነባሩ የኢትዮጵያ እስልምና የሚለው ሃረግ ያለቦታው እና ያለአግባብ እየተተረጎመ እና እየተሰካ ህዝብን ለማደናገር እንዳስፈላጊነቱ የሚስልና የሚዶመዱም ተደርጎ ‹መሰንጠቂያ ማሽን› ይሆን ዘንድ ሆን ተብሎ የተጎነጎነ የጥፋት ሃረግ መሆኑ ግን ለብዙዎቻችን ግልፅ ነው፡፡ ምክንየቱስ ቢባልም እስልምና ነባሩና አዲሱ፤ አፍሪካዊ እና አረባዊ፤ የነጭና የጥቁር የሚል ስያሜ ሊወጣለት የማይችል እምነት ነውና፡፡

II. ነባሩ የኢትዮጵያ እስልምና የሚለው ሃረግ እንዴት ተመዘዘ?
የኢትዮጵያን ታሪክ ያነበበ ቀርቶ ያለፉትን ሁለት መንግስታት የማየት እድል ያገኘ ኢትዮጵያዊ የኛ የሙስሊሞችን ነባራዊ ገፅታ በውል ይረዳል የሚል እምነት አለን፡፡ የእስልምና ሃይማኖት መሰበክ ከጀመረበት ግዜ አንስቶ የአለም ፍፃሜ ድረስ የይዘት ለውጥ እንደማያመጣ እርግጥ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በነበሩባቸው የታሪክ ውጣውረዶች የሚያሳዩዋቸው የአምልኮ አተገባበር፤ ማህበራዊ መስተጋብር፤ ሁለንተናዊ ሃገራዊ ተሳትፎ ግን በሁሉም ዘመናት አንድ አይነት ነበሩ ለማለት አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች ስንባል መኖራችንን የተረዳ ማንም አካል እነዚህ አስተሳሰባዊ ሳይሆኑ ተግባራዊ ልዩነቶች ለምን ተፈጠሩ ብሎም ይጠይቃል ተብሎ አይታሰብም፡፡ በቀደምት ስርዓቶች ሙስሊሙ ሙሉ የሃይማኖት አስተምህሮቱን መተግበር የሚያስችል ነፃነት ነበረው ብሎ መናገር እንደማይቻል ሁሉ ዛሬ ላይ በሙስሊሙ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ላይ የታዩ ለውጦች መብትን ከመተግበር ያለፉ እምነት ነክ የአስተሳሰብ ለውጥ ናቸው ብሎ መሞገትም ከንቱ ነው፡፡ እነዚህ ለውጦች ፈፅሞ መታየት የለባቸውም ብሎ መሞገት ‹‹አዲሲቷ ኢትዮጵያ›› የሚባል ታሪክ የለም ብሎ እንደመሞገትም ይቆጠራልና፡፡ ምክንያቱም የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች የተከበሩባት፣ መልካም አስተዳደር የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለማየት መላው ህዝባችን በነበረው ምኞት ሁሉም ህዝባችን ታግሏል፣ ብዙዎቹም ለዚህ ዓላማ መስዋዕት ሆነዋል፡፡ የዚህ ታላቅ መሰዋዕትነት ፍሬዎች አንዱ የሃይማኖት ነፃነት እንደመሆኑ መጠን የኢትዮጵያ ሙስሊምም እምነቱን ያለመሸማቀቅ እና ያለመሸራረፍ ሙሉ በሙሉ እንዲተገብር የሚያስችል እድል አግኝቷል፡፡
ነባሩ የኢትዮጵያ እስልምና የሚለው ሃረግ በተለይ ከመሪዎቻችን ደጋግሞ ጆሯችን ላይ ሲያቃጭል፤ አንዳንድ ባለስልጣናት በመስጂድ ውስጥ ያደጉ ይመስል እስልምና ወደሃገራችን ከገባበት ግዜ አንስቶ የኢትዮጵያ ሙስሊም ይከተለው የነበረው እንዲህ ያለውን ነው፤ ይሄኛው የእስልምና አስተምህሮ መገለጫ አይደለም በማለት ሃይማኖታዊ ፈትዋ (ብይን) ሲሰጡ መደመጣቸው የተዛባግለሰባዊ አስተያየታቸውን ብቻ ሳይሆን የወከሉት ስርዓት ጓዳ ላይም ትዝብትን የሚያሳድር ነው፡፡ ይህንን ‹ነባሩ› እየተባለ የሚተረክልንን ግን ደግሞ በተጨባጭ በመንግስት እየተያዙ ያሉ አቋሞችና እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ወደ ነባሩ የተሸማቀቀ ማንነታችሁ፤ ወደ ጥንቱ ውስን የእምነት ነፃነታችሁ፤ ወደ ቀድሞው የድብቅ አምልኮአችሁ… ተመለሱ እየተባልን እንደሆነ ተሰምቶን ስጋት ካደረብን ውሎ አድሯል፡፡ ህገ መንግስቱ በፀደቀ ማግስት የመንግስት ልዕልና መሰረቱ የህዝቦች ልዕልና እንደሆነ በመተማመን የተገኘውን ነፃነት በማወቅ እና በመተግበር ላይ ያለውን ሙስሊም ያለበትን ተጨባጭ ወደኋላ በመተው የግል ድብቅ አጀንዳ ያለ በሚያስመስል መልኩ ‹መቻቻል› የሚለውን ቃል የዜጎች መከባበርና መፈቃቀር መሆኑ ቀርቶ አሃዳዊ እምነት መከተል በሚያስመስል መልኩ መገለጫዎቹ የመስቀል ዳመራ ማብራትና የጥምቀት ታቦት መሸኘት ተደርጎ መሳሉ ይህን ያላፀደቁትን ደግሞ ነባሩን የመቻቻል ባህላችንን ያፈረሱ ሲባል ለህገ መንግስቱ የእንጀራ ልጅ ነህ እየተባለ እንደሆነ የሚቆጥረው ሙስሊም ቁጥሩ እያሻቀበ ነው፡፡
III. የመንግስት አቋምን የወለዱ የጥፋት ሃይሎች ተረቶች
እስከ ቅርብ ግዚያት ድረስ ከመንግስት ባለስልጣናትም ሆነ መገናኛ ብዙሃን ከሙስሊሙ የህብረተሰብ ክፍል ለኢትዮጵያ ስጋት ይሆናል ተብሎ የሚታሰብ አመለካከትም ሆነ ተግባር ሲወራ አልሰማንም፡፡ ልንሰማም አይጠበቅም፡፡ ሆኖም ግን የቀድሞዎቹን ስርዓት ከሚናፍቁ፤ የሙስሊሙ ነፃነት ማግኘት ካልተዋጠላቸው፤ አንዳንዴም ጉዳዩን በቅንነት ለመረዳት ፍላጎት ከማጣት የመነጩ በየመንደሩና በየመጣጥፎች ላይ የሚነዙ አጓጉል አስተሳሰቦች ጥቂት ቢሆኑም ሲደመጡ ግን ቆይተዋል፡፡ አብዛኛዎቹ አስተሳሰቦች መነሻቸው የተዛባ በመሆኑ ደግሞ ድምዳሜአቸውም ሚዛኑን የሳተ ነው፡፡ ዋና አላማቸውም በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ሙስሊሙ ያገኘውን ነፃነት ባለመቀበል እና ሙስሊሙን ስጋት አድርጎ በመሳል ሙስሊሙን ወደ ቀድሞ ይዞታው መመለስ ነው፡፡ በዚህም ኢትዮጵያን ወደ ቀድሞው ጥቁር ታሪኳ የመቀልበስ የረዥም ግዜ ግባቸውን እውን ለማድረግ ይታትራሉ፡፡
በነዚህ ጥቂት የመንደር አሉባልታዎች፤ በራሪ ወረቀቶች፤ መፅሄቶች እና አልፎ አልፎ መልክ እና አቅጣጫ ጠቋሚ ሆነው በተዘጋጁ መፅሃፎች ‹‹አክራሪ እስልምና›› የለት ከለት አጀንዳ ተደረገ፡፡ ለባዶ ተረታቸውም ማስረጃ አድርገው የሚያቀርቧቸው ነጥቦች እንደወቅቱና እንደፀሃፊው ቢለያይም የነገሩን አሳሳቢነትና ኢትዮጵያን ከአክራሪነት ሳይሆን ከእስልምና መከላከል የሚመስሉበትን ሁኔታ ለማስረዳት ጥቂቶቹን ብንጠቅስ ‹‹ ቁርአናችን ተቀደደ፤ እስልምና ተናቀ፤ ተገፋን የሚሉ ፕሮፖጋንዳዎችን የሚነዙ፤ የመስጂድ ቦታ ካልተሰጠን የሚሉ፤ የቀደምት ነገስታት እስልምናን ጨቁነዋል የሚል አሉባልታ ደጋግመው የሚያስተጋቡ፤ ንጉስ አስሃማ (ነጃሺ) ሰልሟል የሚሉ፤ ሱሪ ከፍ የሚያደርጉ፤ ፂም የሚያሳድጉ፤ አክሱም መስጂድ ይሰራ በማለት የሚሞግቱ፤ ኢማም አህመድን በጀግንነት የሚያደንቁ፤ የሙስሊሙ ቁጥር አንሶ ነው የተገመተው ብለው የሚከራከሩ እና ሌሎች ለቁጥር የሚታክቱ የኢትዮጵያ ሙስሊም ወደ አክራሪነት እየተቀየረ መሆኑን ማሳያ ተደርገው የተሳሉ ነጥቦች ናቸው፡፡ ከነዚህ በፅሁፍ መልክ ይዘው ከሰፈሩ አሉባልታዎች በተጨማሪ በመኖሪያ መንደሮቻችን፤ በትምህርት ተቋሞቻችን፤ እና በሌሎች የአገልግሎት መስጫ ስፍራዎች በጥቂት የጥፋት ሃይሎች የሚነዙት የአክራሪነት መገለጫዎች ለቁጥር ይታክታሉ፡፡ ‹‹ ጥቁር ተከናንበው የሚሄዱ፤ ዳዕዋ እያሉ መሰባሰብ የሚያበዙ፤ በትምህርት ተቋማት ውስጥ ካልሰገድን የሚሉ፤ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የቅበላና የመሸኛ ፕሮግራሞች የሚያዘጋጁ…..ወዘተ የሚሉ ይገኝባቸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ተጨባጭ የብሄረሰቦች የታፈኑ መብቶች፤ የተገደቡ ነፃነቶች ይፋ ወጥተው ሲታዩ የዴሞክራሲ ፍሬነታቸው ታምኖበት በአዎንታዊነት ይወሳሉ፡፡ የሙስሊሙ የታፈነ ድምፅ መሰማቱ እና የተገደበው የሃይማኖት ነፃነት መገርሰሱ ማሳያ ለሆኑ የአምልኮ ተግባራት ግን በተቃራኒው የአክራረነት መገለጫ ተደርገው ይገለጻሉ፡፡ እነዚህ የመንደር አሉባልታዎችንም ከነእንክርዳዳቸው የመቀበል አዝማሚያ በአንዳንድ ባለስልጣናትና መገነኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ይስተዋላል፡፡ መንግስት አባታዊ ሃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ዜጎች ከሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ውስጥ የዴሞክራሲ ፍሬ፤ የነፃነት መገለጫ፤ መብት የመጠየቅና የመተግበር ባህል መዳበር፤ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ አዲሱ ገፅታ የሆኑትን መለየትና የህብረተሰቡን የተዛባ አመለካከት በህገ መንግስታዊ ማስረጃዎች ማሳመን ይገባው ነበር፡፡ የግለሰቦችም ሆነ የቡድን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በህገመንግታችን ሙሉ ጥበቃ እንደተደረገላቸው በተነገረን ማግስት ፍፁም ነፃ የሆኑ ሃይማኖታዊ ክንዋኔዎች ‹‹አክራሪነት›› ፈፃሚዎቹ ደግሞ ‹‹አክራሪዎች› ተብለው ሲብጠለጠሉ እኔን አይመለከተኝም በሚል ዳር ቆሞ ማየት ብዝሃነትን የሚቀበልና በእኩልነት የሚያስተናግድ ህገ-መንግስት በሙስሊሙ ላይ ሲሆን የተለየ ትርጉም ይሰጠዋል በሚል ስጋት ውስጥ የወደቅን በርካቶች ነን፡፡
ከሙስሊሙም ሆነ ከክርስቲያኑ ወገን ፅንፈኝነት የተጠናወታቸው አልያም ግላዊ እና ቡድናዊ በሆኑ ስህተቶች የሚፈፀሙ ማንም ጤናማ አእምሮ ያለው አካል ሊያወግዛቸው የሚገቡ ጥፋቶች እንዳሉ እናምናለን፡፡ ተግባሩንም በጽኑ እናወግዛለን፡፡ ነገር ግን ሚዛኑን በሙስሊሙ በኩል ባጋደለ መልኩ በማጉላት ‹‹ እስላማዊ አክራረነት›› የለት ከለት የመንግስት አካላት አጀንዳ ተደረገ፡፡ የጅማውን የአብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎ ሙስሊሙ ህብረተሰብ በአንድ ድምፅ እንዳወገዘው ሁሉ የጉራጌ ዞን ስምንት መስጂዶች ቃጠሎንም ህዝበ ክርስቲያኑ በአንድ ድምፅ አውግዞታል፡፡ በእርግጥም ሊወገዙ የሚገባቸው ህገ ወጥ ተግባራት ናቸውና፡፡ መንግስት በህገወጦች ላይ የተለየ እርምጃ መውሰድ ሲጠበቅበትና በሁለቱም ወገን የደረሱ በደሎችን ማስተማሪያ ሊሆን በሚችል መልኩ ለህዝብ ማቅረብ ሲጠበቅበት በክርስቲያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰውን የህግ ጥሰት በማጉላት ሌላኛውን በማደብዘዝ የሚና መደበላለቅ አሳየ፡፡
ከዚህም አልፎ በመንግስት የተዘጋጁ ‹የጥናት ሰነዶች› ለመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት፤ ተማሪዎችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያየ ሽፋን ተላብሶ ለመወያያነት መቅረብ የተለመደ ስራ ሆነ፡፡ መንግስት በጥናት የተደገፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ለአመራሩም ሆነ ለህብረተሰቡ ማቅረቡ አበጀህ የሚያስብልና የመንግስትና የህዝብን አብሮነት የሚያጎለብት ሁነኛ መፍትሄ ነው፡፡ ነገር ግን በነዚህ የመንግስት ‹የጥናት ሰነዶች› የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን አስመልክቶ የተካተቱ በርካታ ነጥቦች አንድም እስልምናን ተንተርሶ በአለም አቀፍ ደረጃ በተነሳው የፖለቲካ ውጣ ውረድ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ያላቸውን አቋም በውል ያላጤነ በሌላ መልኩ ደግሞ ቀድሞ የጥቂት የጥፋት ሃይሎች የመንደር አሉባልታ የነበሩ ‹‹የእስላማዊ አክራሪነት›› መገለጫዎችን ከነእንክርዳዳቸው በመውሰድ ይፋ የአክራሪነት መገለጫ አድርጎ መፈረጁ ለኛ ለሙስሊሞች አስደንጋጭም አሳዛኝም ነበር፡፡ በዚህም አካሄድ ጉዳዩ ጥልቀት ባለው መልኩ አለመመርመሩን ከማሳየት ባለፈ በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ላይ ሌላ የታሪክ ምዕራፍ የተከፈተ የሚያስመስልባቸው ሁኔታዎችም ተስተውለዋል፡፡ ለዚህም እንደማሳያ የሚሆነን ቀድሞ በአሉባልታ ደረጃ ከጥቂቶች ስንሰማ የኖርናቸውን ‹‹በቀድሞ ነገስታት ተጨቁነናል በማለት ማስተጋባት፤ ቁርዓን ተቀደደብን እያሉ ማራገብ፤ ሙሃደራ በሚባል የመንደር አደረጃጀት መሰባሰብ፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቅበላና መሸኛ ፕሮግራም ማዘጋጀት ብሎም በትምህርት የደከሙትን የሚያግዙበት በማስጠናት የመረዳደት ስልት እንዲሁም በምርጫ፤ በስብሰባዎችና በልማት ስራዎች የመንግስት ዋነኛ ደጋፊ መስሎ መቅረብ›› የመሳሰሉና ሌሎች እጅግ አሳዛኝ ነጥቦች ‹‹የእስላማዊ አክራሪነት›› መገለጫዎች ናቸው ተብለው በመንግስት በይፋ ታወጁ፡፡ አብዛሃኛው ህዝበ ሙስሊምም ባሉት የመረጃ መረቦች ባነበባቸው እነዚህ ‹የመንግስት የጥናት ሰነዶች› የመንግስት አቋም የሚወለደው ከመንደር አሉባልተኞች ነው እንዴ ሲል አመክኖአዊ የሆነ ታሪካዊ ጥያቄ አንስቷል፡፡
እነዚህ በየትኛውም አለማዊም ሆነ ሃይማኖታዊ መመዘኛዎች የአክራሪነት መገለጫ መሆን የማይችሉ ኢትዮጵያዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን የመንግስት አካላት በህዝቡ ውስጥ ለማስረፅና ለመከላከል ብለው ወዳመኑት እርምጃ ሲገቡ ጉዳዩ ላም ባልዋለበት ነውና ለብዙሃኑ ህዝበ ሙስሊም ‹ዘመኑ የወለዳቸው ሙስሊሙን ማሸማቀቂያ አጀንዳዎች› ተደርገው መወሰዳቸው አልቀረም፡፡ ለዚህም በቂ አመክኖአዊ ማስረጃ ማቅረብ ይቻላል፡፡ የቀድሞዎቹን የግፍ አገዛዝ እንተወውና የአፄዎቹ ስርዓት መቋጫ ላይ ሙስሊሙ ካገኛቸው ጠባብ መብቶች አንዱ በደረሰበት የስግደት ስርዓቱን መፈፀም ነው፡፡ ይህን መብቱን ለመተግበር ይዞ የሚጓዛቸው ሽርጥና የውሃ መያዣ ጡሌ በየሄደበት ‹ሽርጣምና ጡሌአም› ተብሎ በህብረተሰቡ እንዲሸማቀቅ ይደረግባቸው የነበሩ ነጥቦች ናቸው፡፡ ዛሬ ላይ የተገኘው አንፃራዊ ነፃነት የወለዳቸው የእምነት ነፃነት መገለጫዎች የሆኑ ዳዕዋ(ሙሃደራ)፤ ማህበራዊ ትስስር እና የመብት ጥሰት አቤቱታ የፅንፈኝነት መገለጫዎች ሲባሉ ለብዙሃኑ ሙስሊም ‹የዘመናችን ሙስሊሙን የማሸማቀቂያ አጀንዳዎች› እንጂ ሌላ ተደርገው ሊወሰዱ አይችሉም፡፡ ለምን ቢባል መንግስት ያመጣውን ልማትና ዴሞክራሲ ከቀደምት መንግስታት አንፃር አወዳድሮ ማሳየት የሚወደስ ተግባር ሆኖ ሲወሰድ ሙስሊም ዜጎች ከቀደምት ስርዓቶች አንፃር ያገኙትን ነፃነት በማጉላት መናገርና የቀድሞዎቹን መኮነን የአክራሪነት መገለጫ ሊባል አይገባምና፡፡ ከዚህም አልፎ ‹የተበድለናል አቤቱታ› የአክራሪነት መገለጫነቱን መንግስት ማፅደቁ የበደሉን ህጋዊነት ማመንም ተደርጎ የሚወሰድበት አረዳድም ይኖራል፡፡

IV. ከተሳሳቱ ደምዳሜዎች የመነጩ የተሳሳቱ መፍትሄዎች
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) የተቋቋመው ምንም እንኳ በጨቋኙ የደርግ ስርዓት ቢሆንም አላማዎቹና ጅምር ተግባሮቹ ግን ለታሪክ የሚዘከር ቁም ነገር አላቸው፡፡ በሁሉም ዘንድ ይከበሩ የነበሩት የተቋሙ ጠንሳሽና አመራሮቹ በአርቆ አስተዋይነታቸውና በእውነተኛ አባትነታቸው ሁሌም ይወሳሉ፡፡ እስልምናና ሙስሊሞች የአለም አቀፉ ፖለቲካ አጀንዳ ከመሆናቸው በላይ ከላይ እንደማሳያ ያነሳናቸው ሃገራዊ የተዛቡ ምልከታዎች ባሉበት ተጨባጭ ሁኔታ ተቋሙ ከምን ግዜውም በተሻለ በተደራጀና በህዝብ ተቀባይነት አግኝተው አባታዊ ሃላፊነትን በሚወጡ አመራሮች መወከል ይጠበቅበት ነበር፡፡ ግና ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነ፡፡
የኢስላም አስተምህሮ አክራሪነትንና ፅንፈኝነትን ለመዋጋት በራሱ ከበቂ በላይ ሲሆን ጠርዘኛ አስተሳሰበችንና ጥራዝ ነጠቅ ግለሰቦችን በማረቅ ላይ የሃይማኖት መሪዎች ሚና እጅጉን የጎላ ነው፡፡ የተቋማችን መሪዎች ግን እንደ ሃይማኖት መሪነት ጉዳዩን ከእምነት አንፃር በመተንተንና ነባራዊውን ሁኔታ በጥልቀት በመፈተሽ ሁሉን ያማከለ የውይይት እና የመፍትሄ ማፈላለግ ስራን በመስራት ነገሮችን ፈር ማስያዝ ሲቻል ከህዝበ ሙስሊሙ ተጨባጭ ሁኔታ ይልቅ የመንደር ‹እስላማዊ አክራሪነት› መፈክርን በማንገብ ሙስሊሙን አክራሪ እና ፅንፈኛ ከማለት አልፈው አሸባሪ ብለው ለመፈረጅም ይዳዳቸዋል፡፡ በዚህ በተሳሳተ ድምዳሜ ተነስተውም የተሳሳተ የመፍትሄ ሃሳብ ወለዱ፡፡ ሰዎች የራሳቸውን የእምነት የአስተሳሰብ መስመር እንዳይከተሉ በማስገደድ የራስን የአስተሳሰብ መስመር በሌሎች ላይ ለመጫን መንቀሳቀስ አክራሪነት እንደሆነ እየተወሳ ለእምነቱም ሆነ ለአማኙ ባእድ አስተምህሮን በህዝበ ሙስሊሙ ላይ በመጫን አክራሪነት የመጅሊሱ መገለጫ ባህሪ ሆነ፡፡ የመጅሊስ አመራሮች እንደግለሰብ የፈለጉትን የአስተሳሰብ መስመር የመከተል መብት ቢኖራቸውም በበርካታ አለም አቀፍ ምሁራን ከእስልምና ማፈንገጡ የተነገረለትን የአብደላህ አልሃረሪን የአስተሳሰብ መስመርን ሌሎች የአስተሳሰብ መስመሮች የተሳሳቱ ናቸው በማለት እሱ የሚከተለውን ስርዓተ ሃይማኖት ከማስተማር ባለፈ ከዚህ ውጪ ያሉ መስመሮችን የሚከተሉትን ‹‹ወሃብያ›› ብሎ በመፈረጅ ለኢማምነት አይበቁም፤ ለመድረሳ አስተማሪነት አይመጥኑም በማለት ህዝብን ወደማስቆጣት ድርጊት ተሸጋገረ፡፡ ከዚህ ቀደም የመጅሊስ አመራሮች ‹‹ወሃብያ›› በሚባል ምናባዊ አካል የሰየሙት እዚህ ግባ የማይባሉ ጥቃቅን እምነት ነክ ልዩነቶች የሚያሳዩ ግፋ ሲልም ህገወጥ ስልጣናቸውን የሚቃወሙትን ማጠልሻ ይሆናቸው ዘንድ ነበረ፡፡ ዛሬ ላይ ግን የስልጣን ሹመታቸው ከመጅሊስ ጽ/ቤት የሆነ የሚያስመስሉ አንዳንድ ባለስልጣናትም ጭምር የስልጣንና የነዋይ ፍቅር እምነታቸውን እንዲሸጡ ያደረጋቸው የመጅሊስ አመራሮች በቀደዱለት የጥፋት ቦይ ለመፍሰስ ያልፈቀደውን ህዝበ ሙስሊም ሁሉ በጅምላ የሚጠሩበት ስልታዊ የማግለያና የማሸማቀቂያ ስያሜ ሆኗል፡፡ በነዚህ ሁላ ሂደቶች ውስጥ ግን ህዝቡ መጅሊስንና አስተምህሮቱን በስውር እና በተበጣጠሰ መልኩ ከማውገዝ አልፎ ወደ መንግስት የተሰነዘረ የጣልቃ ገብነት ወቀሳ እምብዛም አልነበረም፡፡

V. የመርህ ይከበር ሃገራዊ ህዝባዊ ተማፅኖ
መጅሊስ መራሹ የአህባሽ አስተምህሮ በየደረጃው ላሉ የመጅሊስ አመራሮች ብቻ በመሰጠት ይቆማል ተብሎ ሲጠበቅ ህብረተሰቡን እስከ ታች ድረስ በመውረድ ለማሰልጠን የተያዘውን ዕቅድና አስፈላጊ ዝግጅት በመገናኛ ብዙሃንና በዒድ አደባባይ ሳይቀር ይታወጅ ጀመር፡፡ በአተገባበር ሂደትም በየመድረኩ የታዩ እንግዳ አስተምህሮዎች የእምነቱን ክብር ያጎደፉና የአማኙን መብት የተጋፉ ግልፅ ህገወጥ ተግባራት በተጨባጭ ታይተዋል፡፡ የመጅሊስ አመራሮችና አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት የሸኽ አብደላህ አልሃረሪን በነባሩ የኢትዮጰያ እስልምና ፈለግ የጠለቀ እውቀት ያላቸው መሆናቸውን ሽንጣቸውን ገትረው መከራከራቸው ለምን ብለን እንድንጠይቅ አስገድዶናል፡፡ ቀድሞውኑ ያለህዝብ ይሁንታ በህዝበ ሙስሊሙ ላይ በግድ ተጭነው ያሉት የመጅሊስ አመራሮች አይደለም የሃይማኖቱ ሊቃውንትን የእውቀት ጥልቀትና እውነተኝነት ለማረጋገጥ፤ እጅግ መሰራተዊ የሚባሉ የሃይማኖቱ ድንጋጌዎችን በወጉ ማወቃቸውን የሚጠራጠሩት ብዙዎች ናቸው፡፡ በየመድረኩ የሸኽየውን የእውቀት ምጥቀትና በመላው አለም የሚሰበከው እርሳቸው ያስተማሩት ፈለግ እንደሆነ፤ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሲያስተምር የነበረው ሙስሊሙ በነባሩ እስልምና ላይ ያለውን እውቀት ከፍ ለማድረግ ነው ሲሉ በአስተምህሮቱ እና በአተገባበሩ ላይ ያሉትን ፍፁም ከኢስላም ያፈነገጡ አስተሳሰቦች የቀድሞው ሙስሊም እምነት በማለት ሊያሳምኑን የሚሞግቱት የመንግስት ሹመኞች ግን ምንጫቸው ከወዴት ግባቸውስ ወዴት እንደሆነ መለየት ተስኖናል፡፡ እምነታችንን ለመበረዝ የተከፈተብንን ጥቁር ዘመቻ ስንቃወምም ለአክራሪነት አስተሳሰባቸው ቦታ እንዳያጡ ብዙሃንን ከመማር መብት የሚያግዱ ተባልን፡፡
የመጅሊስ አመራሮች እንደገለፁት ከመንግስት አካላት በተለይም ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ባደረግናላቸው ግብዣ መሰረት የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች በስልጠናው ላይ በመገኘት ህገ መንግስት አስተምረዋል ሲሉ ተደመጡ፡፡ በስልጠናዎቹ መድረኮች መንግስትን በመወከል ከተገኙ አካላት የተደመጡ ንግግሮች ህገ መንግስት የማስተማርን ድንበር ዘለው መገኘታቸው ለጥቂቶች የመንግስት ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ተደርጎ ቢታይም ለብዙሃኑ ሙስሊም ግን በመጅሊስ የተሳሳተ መረጃ የተመሩ ‹አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት› ግዜአዊ ስህተት ተደርጎ ነበር የተወሰደው፡፡ በወቅቱ የሚያመዝነው እውነታም ይኸው ነበር፡፡ በመጅሊስ እየተፈፀመ ያለው በየትኛውም መመዘኛ ለድርድር በማይቀርበው የእምነት ነፃነት ጥሰት እና በውይይት መድረኮች የተንፀባረቁ እሳቤዎች የማይገናኙ በመሆናቸው ህዝበ ሙስሊሙ የመርህ ይከበር ይፋዊ ተማፅኖውን በመላ ሃገሪቱ ማሰማቱን ቀጠለ፡፡ ከተደረጉና በመደረግ ላይ ካሉ የተማፅኖ ጥሪዎች አንዱ በአዲስ አበባ በተለይም በአወሊያ በመካሄድ ላይ ያለው የ‹መብት ጥሰት ይቁም› ይገኝበታል፡፡
ህዝበ ሙስሊሙ ያነሳውን የመብት ጥያቄ ተከትሎ በመንግስት ይፋ አስተባባሪነት በርካታ የውይይት መድረኮች፤ የተለያዩ መግለጫዎች ተሰጥተዋል፡፡ በነዚህ ወቅቶች ግን ከተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናትና መገነኛ ብዙሃን የተደመጡ ነገሮች መንግስት በጉዳዩ ላይ ያለውን ግልፅ አቋም ከማንፀባረቅ ይልቅ በመጅሊስ የተፈጠረውን ውዥንብር ይበልጥ በማስፋት ህዝብን ግራ የሚያጋቡ ሆነው ነው የተገኙት፡፡ ከፊሎቹ ዘገባዎች እና የውይይት መድረኮች ‹ በአሁኑ ወቅት በሃገራችን ትርጉም ያለው የአክራሪነት ፍላጎት አለ ብሎ መደምደም አይቻልም› ሲሉ ከፊሎቹ ደግሞ ‹ወታደራዊ ክንፍ ያለው የእስልምና አክራሪ አደረጃጀት በሃገራችን በተጨባጭ ይገኛል› ሲሉ በመላው አለም የሚገኙ የፀረ ሽብር ታጋዮች ከየትኛውም ሃገር ይልቅ ወደ ኢትዮጵያ ቀድመው ሊዘምቱ ይገባ ነበር የሚያስብል የተጋነነ ድምዳሜ ነበራቸው፡፡ በዚህም ህዝበ ሙስሊሙን ለእምነቱ ባዳ ለሃገሩም እንግዳ የሆነ እስኪመስለው ድረስ ፍፁም የሚጣረሱ ጉዳዮች ተናፈሱ፡፡ ጨቋኙ የደርግ ስርዓት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ይታገል የነበረውን የኢህአዴግ ሰራዊት በህዝቡ ውስጥ ጭራቅ አስመስሎ በመሳል በተለያዩ ስያሜዎች ህዝብን ያደናግር እንደነበር ማንም ኢትዮጵያዊ አይዘነጋውም፡፡ በዛሬ በሙስሊሞች ጉዳይ ተጨባጭ ሁኔታ የአህባሽን አስተምህሮት የሚቃወሙና መብታችን ይከበር በማለት አቤት የሚሉትን ሁሉ ‹ወሃብያ› በማለት ቀንድ እና ጥርስ ያለው ህዝብ ጨራሽ ጭራቅ አድርጎ ለህዝብ ማቅረብ ያረጀና ያፈጀ ስልት ነው፡፡ ከዚህም በላይ የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት መከበር፤ ዜጎች ጥቅማቸውንና መብታቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ማራመድ፤ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ባህል መፍጠር የሚያስችል ስርዓት ተገንብቷል ተብሎ በታመነበት በዚህ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ዘመን የመብት ጥያቄን ‹አክራሪነት› እና ‹ፀረ-ህገመንግስት›› የሚያሰኝ ምንም በር የለም፡፡
የመብት ጠያቂዎች ስብስብን አስመልክቶ በተለይም የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት አካባቢ በመጅሊስ አመራሮች እና አንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን የተሰጡት ስያሜዎች ከተሰብሳቢዎቹ ማንነትም ሆነ ከተጠየቁት ጥያቄዎች ጋር ምንም የማይዛመድ ነበር፡፡ ‹‹የግል ጥቅም ፈላጊዎች፤ ድብቅ አጀንዳ ያላቸው፤ የተማሪዎችን ጥያቄ አንተርሰው የተሰባሰቡ ፅንፈኞች›› እና የመሳሰሉት የህዝቡን ቁስል ከማዳን ይልቅ እያመረቀዙት የስቃይ ጩኸቱ ይበልጥ እንዲበረታ አደረጉት፡፡ ከዚህ በተቃራኒ መንግስት በጉዳዩ ላይ ህዝቡን ለማወያየት ባደረጋቸው ሙከራዎች የብዙሃኑን ስሜት በትክክል ያደመጠ ቢመስልም ‹መጅሊስ ተሳስቷል› ከማለት ይልቅ ‹ሙስሊሙ አማኝ ተሸውዷል› የሚል ድምዳሜ ላይ መድረሱን የሚያሳዩ አመላካች ነገሮች ነበሩ፡፡ በዚህም የህገመንግስት ሉአላዊነት የሚረጋገጠው በህዝብ ሉአላዊነት እንደሆነ የሚያምነው ኢህአዴግ፤ የሚወስናቸው ሁሉም ውሳኔዎች ከህዝብ ጥቅም አንፃር እንደሚቃኛቸው ያስረዳን መንግስት፤ ከራስ በላይ የህዝብ ጥቅምን ማስቀደም ለዚህም ሲባልም ብዙ መስዋዕትነትን መክፈል እንደሚገባ አምናለሁ ያለን ኢህአዴግ በሙስሊሙ አጀንዳ ሲሆን ከህዝብ በላይ ለህዝብ የማውቀው እኔ ነኝ በሚሉ ባለስልጣናት በየመድረኩና በየሚዲያው ተወክሎ ስናገኘው በመንግስታችን መዋቅር ውስጥ በወሳኝ ሃገራዊ አጀንዳዎች ላይ እንዲህ ዓይነት አመራሮች መኖራቸው ልባችንን ነክቶታል፡፡ የነዚህን ሚዛን የሳቱ አመራሮችን አቋም በመንተራስ ‹‹የመብት ጠያቂዎቹ ፅንፈኞች ናቸው፤ መንግስትም ከጎናችን ነው›› የሚሉ ማስፈራሪያዎች የመጅሊሱ የዘወትር መፈክሮች ሲሆኑ ‹‹ጥያቄዎቻችን ህጋዊ ናቸው፤ ፈጣሪም ከጎናችን ነው›› የሚሉ ድምፆች ደግሞ በህዝቡ ወገን በረቱ ፡፡ አግባብ ያልሆነ ስልጣንን ከሚሸሸው ኢስላማዊ ስብዕና በተፀራሪ የስልጣን እድሜአቸውን ለማራዘም፤ የውስጥ ችግራቸውን ለመሸፈን የሚራወጡት የመጅሊስ አመራሮች በአንዳንድ ባለስልጣናት አይዞህ ባይነት የልብልብ በማግኘት የብዙሃኑን የመብት ጥያቄ በህዝብ የተተፉ ፀረ ሰላም ሃይሎች የሚነዙት አሉባልታ ነው ለማለት ያዘጋጇቸው የፕሮፖጋንዳ ፕሮግራሞች ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ሁኔታ በህዝቡ ተቀባይነትን ማግኘት አልቻሉም፡፡ አሁንም ህዝቡ ተታሎ ይሆን? ከዚህ በተቃራኒ ‹ጥያቄአችሁ የኛም ጥያቄ ነው እና ዝርዝር አካባቢያዊ የመጅሊስ በደሎችን የሚያትቱ አቤቱታዎችና የተቃውሞ ፊርማዎች ከመላ ሃገሪቱ ይጎርፍ ጀመር፡፡ አንዳንድ አካላት ግን ዛሬም ህዝብ ተታሎ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ የሁሉ ነገር መሰረት የሆነው ህዝብ ስንቴ ይሳሳት ይሆን?

VI. መንግስት የዜጎችን ጥያቄ የማድመጥ ግዴታ አለበት
በአንድ በኩል የመጅሊስ ውንጀላዎች መበርከት በሌላ በኩል የተለያዩ አካላት ፍርደ ገምድል ብይኖች ካነሳቸው ጥያቄዎች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው የሚተማመነው መብት ጠያቂው ህዝበ ሙስሊም ለጥያቄዎቹ መልስ ያፈላልጉለት ዘንድ በወከላቸው ኮሚቴዎች አማካኝነት የተለያዩ የመንግስት መስሪያቤቶችን በር አንኳክቷል፡፡ በነዚህ ሂደቶች ውስጥ ሳይጠቀሱ የማይታለፉ ነጥቦች አሉ፡-
ህዝበ ሙስሊሙ የመብት ጥሰቶቹ መንስኤ ሙሉ በሙሉ የመጅሊስ አመራሮች እንደሆኑ ያምን ነበር
መልስ ለማግኘት የሚቻለው በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ብቻ ነው ብሎ አምኖ ተንቀሳቅሷል፡፡
ከጥያቄዎቹ ፍትሃዊነት፤ ግልፅነትና መልስ ለመስጠት ካላቸው ቀላል ይዘት አንፃር ፈጣን ምላሽ ማግኘት ቢቻልም የተሰጡትን ረዣዥም ቀጠሮዎች በትእግስት በመጠባበቅ ለህግ ያለውን ተገዥነት በተግባር አሳይቷል
መልስ ይነገርበታል ተብሎ በሚገመተው የመሰብሰቢያ ስፍራ በቋሚነት በመገኘት ለጥያቄዎቹ መመለስ ያለውን ፅኑ አቋም አሳይቷል
ከላይ ካነሳናቸው ነጥቦች ተቀራራቢ በሆነ መልኩ ከመጅሊስ የተለመዱ ውንጀላዎች በስተቀር ቀድሞ የነበሩት የአንዳንድ ባለስልጣናት የተሳሳተ ውንጀላ እና የተዛቡ ሚዲያ ዘገባዎች ጥያቄዎቹ ቀርበው የምላሽ ቀጠሮ እስከተሰጠበት ድረስ ባሉት ግዜያት ቢያንስ ጋብ ያሉበት ወቅትም ነበር፡፡
በሂደቱ በመንግስት በኩል ከተንፀባረቁት አቋሞች ውስጥ:
ጥያቄዎቹን ለማድመጥ ያሳየው ቁርጠኝነት
የጥያቄዎቹን አግባብነትና እንደ መንግስት መልስ የሚሹ መሆናቸውን እምነት ማሳደሩ
ጉዳዩን በጥልቀት ለማየትና ሰፊ ግዜ በመውሰድ ምላሽ ለመስጠት ቃል መግባቱ
ህዝቡ ለወከላቸው አካላት ተገቢ ካልሆኑ ስያሜዎች መቆጠብና ኮሚቴውን ህገወጥ ማለት ከኮሚቴው ጋር የሚወያየውን መንግስትንም መስደብ ነው የሚል ቁርጠኛ አቋም መያዙ
የመብት ጥያቄ ሂደቶቹ ሰላማዊ መሆናቸውን መመስከር ከብዙዎቹ ጥቂቶች ናቸው፡፡
ይሁንና የሂደቶች ማማር የውጤት ማማርን ያመጣል ተብሎ ቢታመንም በእኛ ተጨባጭ ግን ምላሽ የሚጠበቅበት የየካቲት 26/2004 ቀጠሮ ብዥታ የተሞላባቸው ንግግሮች፤ ከጥያቄዎቹ ግልፅነት በተፃራሪ በአሻሚና አተገባበራቸው ከህዝቡ ፍላጎት ተፃራሪ በሆኑ ውሳኔዎች የተሞላ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ የቅሬታ አቤቱታ ለሚመለከተው አካል የገባ ሲሆን ጥያቄዎቹ ተጨባጭ ምላሽ ይፈልጋሉና ለቀጣይ የስልጣን እርከኖች ቀረቡ፡፡

VII. ለፌ/ጉ/ሚ/ር ሲቀርብ ህጋዊ የተባለ ህዝብ ለጠ/ሚ/ር ሲቀርብ ህገወጥ ሊሆን አይችልም!
ህዝበ ሙስሊሙ ላለፉት ሃያ አመታት ምንም አይነት በእምነቱ ላይ የደረሰበት በደል የለም ለማለት አይቻልም፡፡ ሆኖም ግን በጉዳዮቹ ላይ የመንግስት ቅርብ ድጋፍና ክትትል አልተለየውምና ገኖ የወጣበት አጋጣሚ እምብዛም አልታየም፡፡ አንድ ህዝብ ምደራዊ ድሎቱን የሚቀንሱ፤ ግለሰባዊ ፍላጎቱን የሚቀናቀኑ የመብት ጥሰቶችን እስከመጨረሻው ሊችላቸው አልያም እስኪስተካከሉ ሊታገሳቸው ይችል ይሆናል፡፡ ነገር ግን አማኝ በመሆንና ባለመሆን መካከል የሚገኙ ትላልቅ ገመዶች ሲበጠሱበት ግን ከነርሱ ቀድሞ የእርሱ እስትንፋስ መቆምን ይሻል፡
ጥያቄዎቹን፤ አቅራቢዎቹንም ሆነ አቀራረባቸውን አስመልክቶ ለመንግስት አካላት ከቀረቡበት ግዜ አንስቶ እስከ የካቲት 26 ባሉት ግዜያት የተሰነዘሩ ክሶች፤ የተለጠፉ አፍራሽ ስያሜዎች በተለይ ከመንግስት አካል በይፋ አልተሰማም፡፡ የጥያቄዎቹን አለመመለስ ግልፅ በሆነ አቤቱታ አቅርቦ በጥያቄዎቹም፤ በጠያቂዎቹና በአቀራረቡ ምንም አይነት የይዘት ለውጥ ሳይኖር ከ የካቲት 26 በኋላ ግን ከተለያዩ መስመሮቸ ፍፁም የማይጠበቅ እና ህዝብ በመንግስት ላይ ያለውን አመኔታ የሚንድ አፍራሽ ፕሮፖጋንዳዎች ተደመጡ፡፡ ለነዚህ ፕሮፖጋንዳዎች ደግሞ የፊት አውራሪነቱን ሚና በመጫወት ላይ የሚገኘው የፌ/ጉ/ሚ/ር የተለያዩ የስራ ሃላፊዎች በመገናኛ ብዙሃን የሰጧቸው መግለጫዎችና ቃለመጠይቆች ናቸው፡፡ ለአብነት ያህልም የመጋቢት 9 ሪፖርተር ጋዜጣ ከሚ/ሩ ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም ጋር ያደረገው ቃለምልልስ ያስነበባቸው አቋሞች ግርምትንና ትዝብትን የፈጠሩ ክስተቶች ናቸው፡፡
የስራ ሃላፊዎቹ በተለይም የፌ/ጉ/ሚ/ር ሚኒስትሩ የነዚህን ግልፅ የመብት ጥሰት ጥያቄዎች ከዚህ ቀደም በይፋ አግባብነት ያላቸው ሲሉ እንዳልተደመጡ እና ጠያቂውንም ህዝበ ሙስሊም ሰላማዊነቱን መመስከራቸውን የዘነጉት በሚያስመስል መልኩ ‹‹አሁን ለመጨረሻ ግዜ ምሽጋችን ተመታ ማለት ነው፡፡ ይኼ ተመታ ማለት የአይዲዮሎጂው መፍለቂያና ማስተማሪያ ማዕከልና የእኛ ህልውና አበቃ ማለት ነው በሚል ነው የመጨረሻ የሞት ሽረት አድርጎ የመንቀሳቀስ ስራ ውስጥ እየተገባ ነው ያለው›› ሲሉ አዲስ አበባ በአንድ ቦታ ብቻ የሚሰበሰቡ መቶ ሺዎችን ማብጠልጠል ቢዳፍሩም በመላ ሃገሪቱ መሰል ተቃውሞ ይዘው ቢሯቸውን ላንኳኩ የክልል አቤቱታ አቅራቢዎች ግን ያሉት ነገር አልነበረም፡፡ ከየካቲት 26 በፊት ሰላማዊ የነበረው ህዝበ ሙስሊም በሳምንታት እድሜ እንዴት ወደ ‹ምሽጉ የፈረሰበት ፅንፈኛ› ሊቀየር እንደቻለ ለሰሚው ግራ ነው፡፡ እንደፀሃይ ብርሃን ፍንትው ያሉት እጅግ ግልፅ ጥያቄዎችስ በምን አይነት አተረጓጎም የእስላማዊ መንግስት ማቋቋ ተብለው ሊወሰዱ እንደሚችሉ ማንም ሊረዳው አይችልም፡፡ በሃላፊዎቹ የተነገሩት እጅግ አደገኛ ነጥቦች በሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን በሌሎች እምነት ተከታይ ወገኖቻችን ልብ ውስጥ ሊፈጥር የሚችለው ውዥንብር እና እሱን ተከትሎ ሊመጣ የሚችለው ህዝባዊ ቀውስ ሃያል በሆነ ነበር፡፡ የጥያቄዎቹን ግልፅነትና ይዘት አቅራቢው ህዝበ ሙስሊም በተረዳበት መጠን የሌሎች እምነት ወገኖች መረዳታቸው በአቅራቢዎቹና በጥያቄዎቹ ላይ የታየውን ቅፅበታዊ የአተረጓጎም አደገኛ ለውጥ መሰረተ ቢስነት በተግባር ሊረጋገጥ ችሏል፡፡ አመራሩ የህዝብ የሰላ ጫፍ ሆኖ አርቆ ማስተዋል ሲጠበቅበት የብቃት ማነስ በታየባቸው የመንግስት ተወካዮች ብናፍርም ህዝብ የዲፕሎማቲክነቱን ሚና ሲወጣ ማየት ግን በዜግነት የሚያኮራ ታላቅ ብስራት ነው፡፡
መረሳት የሌለበት ሌላውና ትልቁ ነጥብ ደግሞ ሚ/ር መ/ቤቱ በሃገሪቱ ከሚገኙ የስልጣን እርከኖች አንዱ እንጂ ብቸኛና የበላይ አይደለም፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ የእምነቴ ህልውና ነው ብሎ በሚያምንበት ነጥብ ላይ በተካሄደው የመብት ጥሰት እንዲቆም ጥያቄዎቹን ለጠ/ሚ/ር ጽ/ቤት አቅርቦ መልሱን እንደከዚህ ቀደሙ በትእግስት በመጠባበቅ ላይ ሳለ በምን እይታ ህገወጥ ሊባል ይችላል፡፡በእርግጥ የስልጠናው መባቻ አካባቢ የተለያዩ ባለስልጣናት በይፋ የተናገሩትን አስተምህሮቱን መቃወም በህግ ተጠያቂ የሚያደርግ ህገ ወጥ ተግባር መሆኑን የሚያስይዙ ንግግሮች በርካታ ቢሆኑም የባለስልጣን ስህተት በእምነታችን ላይ እንድንፈርድ ስለማያደርገን በይፋ ወደ ተቃውሞ ገብተናል፡፡ ባለስልጣናቱ እንደተናገሩት ‹‹ስልጠናውን መስጠት ያስፈለገው እምነታቸውን አጥብቀው የያዙ መስሏቸው ሳያውቁት በአክራሪነትና ፅንፈኝነት መረብ ውስጥ እየተገፉ የገቡ በመኖራቸው እነሱን ‹‹ወደ ቀጥተኛው እስልምና›› ለመመለስ እንጂ ‹‹እንደ ወሃብያ ያለ ወሮበላን አስር ቤት ለማጎር›› ስልጠና አስፈላጊ አለመሆኑን፤ በዚህም ስልጠና‹ምዕመኑን ወደ ‹ቀጥተኛው እስልምና› ሊመሩት እንደሆነ ከፖለቲካ መፃህፍት የተቀመመ ሃይማኖታዊ ትንታኔ በመስጠት የስልጠናውን አላማ ጥርት ባለ ቋንቋ አስረድተውናል፡፡በባለስልጣናቱ ‹‹ወሃብያ›› ተብሎ የተፈጠረው ማደናገሪያ ስያሜ ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ይሏታል ጅግራ እንደሚሉት ብሂል በመጅሊስና አጋሮቹ የጥፋት ወጥመድ አልያዝ ያለውን ህዝበ ሙስሊም መጠሪያ ተደርጎ በመወሰድ ላይ ይገኛል፡፡
ሌላውና ላለፉት ወራት ከፌ/ጉ/ሚ/ር በጎ ምላሽ ለማግኘት ህዝበ ሙስሊሙ ያሳለፋቸውን ግዜያት በከንቱ እንደበባከኑ ያስቆጠረው ጉዳይ የሚ/ር መ/ቤቱ የስራ ሃላፊዎች አህባሽ የተባለውን አስተምህሮ ከመጅሊስ ጋር በመተባበር ለመስጠት ተገደናል ሲሉ መደመጣቸው ነው፡፡ [A1] አመት ሊሞላው ጥቂት ወራት የቀሩት የመብት ጥሰት ከተጀመረ አንስቶ መጅሊስ በደለኝ፤ በመጅሊስ የተሳሳተ መረጃ አንዳንድ የመንግስት ባለስልጣናት ጣልቃ ገብነት ታይቶባቸዋል ሲል ለነበረው ህዝበ ሙስሊም ከባድ መርዶ ነገሩት፡፡ በአንድ በኩል የበርካታ ባለስልጣናት በስልጠናዎቹ ወቅት ህገመንግስትን ከማስተማር እና ፀጥታ ከማስጠበቅ የዘለለ ሚና አልነበረንም መባሉን የሻረ ግልፅ አንድን አስተምህሮ የማስፋፋት ሃላፊነት መ/ቤቱ ሲወስድ ተበዳዩን ህዝበ ሙስሊም ክስህን በመጅሊስ ላይ ሳይሆን በፌ/ጉ/ሚ/ር ላይ አነጣጥር የሚል ከባድ መልእክት አስተላልፏል፡፡ ዛሬ ላይ ቆም ብለን ስናስበው ፌ/ጉ/ሚ/ር ለህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ሊኖረው እንደማይችልም መረዳት ከነበረብን ግዜ በጣም መዘግየታችንን አውቀናል፡፡ የረፈደ ቢመስልም ዛሬ ግን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ዳግም ላንማፀን ለጥያቄአችን ትክክለኛ መልስ ከምንጠብቅበት የመንግስት የስልጣን እርከን ተሸጋግረናል፡፡
ይህን ምክንያቱ ያልታወቀ የአስተምህሮት መረጣ ውስጥ ገብተናል ነጋሪት መጎሰምን ተከትሎ ህዝበ ሙስሊሙ ላይ ሁለት አይነት አስተሳሰብ መስረፅ ጀመረ፡፡ በአንድ በኩል ጉዳዩን ተጋፍተን የማንዘልቀው የማይከሰሰውና የማይገሰሰው መንግስት ጋር መላተም ነው ሲሉ በሌላ መልኩ እና አብዛሃኛው ህዝበ ሙስሊም አቋም ግን ህግ ባለበት ሃገር ማንም ህገወጥ እንዲሆን አይፈቀድለትምና አማኞች ተስፋ አይቆርጡም ብለን በጥያቄአችን እንገፋለን የሚል ነው፡፡

VIII. መንግስት በጉዳዩ ላይ ያለውን ግልፅ አቋም ያሳውቀን
ከላይ እጅግ በጥቂቱ ለማየት እንደሞከርነው ኢህአዴግን ወክለው በየመድረኩ የተገኙት ባለስልጣናት ያሳዩት የተደበላለቀ አንዳንዴም ጥላቻና ንቀት የተሞላበት ጣልቃ ገብነት ዛሬም ላይ የመንግስት ትክክለኛ አቅጣጫ ነው ብለን ከመውሰዳችን በፊት በይፋ ለመስማት የምንጠብቀው ሌላ የስልጣን እርከን እንዳለ ይሰማናል፡፡ እነኚሁ ባለስልጣናት በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የፓርቲያቸውን ትክክለኝነት ከሚያስረዱበት እጅግ በተሻለ ፅናት የአብደላህ አልሃረሪን አስተምህሮ ትክክለኝነትና የነባሩ የኢትዮጵያ እስልምና ገፅታ አድርገው ለመጋት መሞከራቸው በእምነታችን ላይ መሳለቅ ብቻ ሳይሆን በታሪካችን ላይም ማፌዝ ነውና ዳግም ላይነሳ ይብቃ እንላለን፡፡ ጉዳዩ የእምነት ህልውናን ያዘለ ቀይ መስመር ነውና የሃሰት ፕሮፖጋንዳ በየትኛውም ምድራዊ በሆነ ከፍተኛ በሚባል የስልጣን እርከን ላይ ባለ አካል ቢደጋገም ነገሩን እውነት ሊያስብለው የሚችልበት በር ላይከፈት ከተዘጋ የኒያ ታላቅ ነቢይ የነብዩ መሐመድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) እና የባልደረቦቻቸው እንዲሁም ከእርሳቸው በኋላ ቅኑን መንገድ የተከተሉት ትውልዶች የህይወት ታሪክ አስተምሮን አልፏል፡፡ በነብዩ ሙሐመድ (የአላህ ሰላትና ሰላም በእርሳቸው ላይ ይሁን) ‹የእስልምናን መንገድ እንድተው ፀሃይን በቀኝ እጄ ጨረቃን ደግሞ በግራ እጄ ላስቀምጥልህ ቢሉኝ እንኳ አላህ እውነትን እስኪያሰፍን አሊያም እስከ ሞቴ ፍንክች አልልም› የተባለለት የእውነት ጎዳና እስልምና ዛሬ በመጅሊስ አመራሮች በሽራፊ ሳንቲም ገበያ ላይ ወጥቷል፡፡ ድንበር ባለፉ ባለስልጣናትም ከአንድሺህ አራት መቶ አመት በፊት ሰዎች ህይወታቸውን የሰዉለት ቀያቸውን ጥለው የተሰደዱለት እስልምና የሸኽ አብደላህ አልሃረሪ ፈለግ ነው መባል የእስልምናን እውነተኝነት እንደ መንግስት ያፀደቀች የመጀመሪያዋ ሃገር ኢትዮጵያ ዛሬ ደግሞ አስተምህሮቱን በማጥላላት የመጀመሪያዋ ልትሆን ይሆን ያስብላል፡፡ ይህን ለማለት ግን አሁንም የቀረን የስልጣን እርከን አለና መንግስት ሊከተለው በሚችለው በማንኛውም የውስጥ አሰራር ድንበር ያለፉትን ባለስልጣናትን በማረም ፍትህን በሰላምና በትዕግስት እየጠበቀ ላለው ህዝበ ሙስሊም አቋሙን ግልፅ ያድርግልን እንላለን፡፡ የህዝብን ቅሬታ መስማት ውለታ ሳይሆን የመንግስት ትልቅ ስራ ነውና መንግስት ግዴታውን ይወጣ፡፡

IX. ሙስሊሙን ያለአግባብ በስጋት መፈረጅ፤ ማዋከብና ማሸማቀቅ በአፋጣኝ ይቁምልን
ከላይ ባነሳናቸው እጅግ በጣም ጥቂት ነጥቦች መንግስት ‹‹የጥናት ሰነድ›› እያለ በየመድረኩ የሚያቀርባቸው ፅሁፎች በአጠናን ስልትም ሆነ በመረጃ ተዓማኒነታቸው ጉድለት ‹ጥናት› የሚባለውን ደረጃ ፈፅሞ ሊያገኙ የማይገባቸው እንደሆኑ መረዳት አያዳግትም፡፡ እነዚህ በሳይንሳዊ ዘዴ ያልተተነተኑ፤ መረጃቸው ተበጥሮና ተነፍቶ እውነታው ከእንክርዳዱ ያልተለዩ ‹ምነው ምሁር አለቀ እንዴ› የሚያስብሉ ‹ጥናት› ተብለው በቀረቡ የአናቅፅ ስብስቦች ፣የአክራሪ እስልምና› መገለጫዎች ተብለው የተነገሩን በዛሬው የመረጃ ትስስር አለምን አንድ ባደረገበት ዘመን ቀርቶ በድንጋይ ዳቦ ዘመንም አድማጭ ያገኛሉ ብሎ መገመት ያዳግታል፡፡ አንዳንድ ባለስልጣናት የህገመንግስት፤ የፖሊሲና እስትራቴጂ አተገባበር የሚያግዙ መፃህፍትና ጥናቶችን ሳይሆን በአረበኛ የተዘጋጁ የእስላማዊ መፃህፍትን ከጫፍ እስከጫፍ አገላብጠናል በሚያስብል ድፍረት በቀጥታ እንደነገሩን የአብደላህ አልሃረሪ ፈለግ የሚሰብከው ‹የአክራሪነት አስተሳሰብን በቅዱስ ቁርዓንና ሃዲስ አስተሳሰብ ቀይረው ማስተማር ነው› ብለውናል፡፡ ግና የእምነቱ ባለቤቶችና በውስጥ ያሉ የእውቀት ባልተቤቶች ብቃቱ ስላላቸው ብቻ ሳይሆን ክብራቸውም ስለሚፈቅድላቸው በአብደላሀ አልሀረሪ አቋም ላይ ፈትዋ ሰጥተዋል፡፡ የሸኽየውን አስተምህሮ ዘመን ተሸጋሪውን እስልምና ለሁለቱም አለማት ፈጣሪ ሳይሆን ምድራዊ ስልጣንን ለተቆናጠጡ እንደ መጅሊስ አመራር ላሉ የስልጣንና የነዋይ አፍቃሪዎች እንዲሆን በርዘውና ከልሰው አዘጋጅተውታል፡፡ ይህም አስተሳሰብ የአቋማቸው ተቀናቃኝ ለሆነው ህዝበ ሙስሊም መድፈቂያ የተዘጋጀ ‹የተጠና ሌላ አዲስ ሃይማኖት› እንደሆነ በማይናወጥ መረጃ አስረግጠዋል፡፡
የፅንፈኝነት አስተሳሰቦችና ድርጊቶች እንዳይባባሱ መንግስት ህግ በማስከበሩ ረገድ ካለው ሚና ባልተናነሰ ሁኔታ የሃይማኖት ተቋማትም ወሳኝ ሚና መጫወት ይገባቸዋል ብለን እናምናለን፡፡ የሃይማኖት ተቋማቱ አክራሪነትን በብቃት ለመከላከል የሚቻላቸው ግን በቅድሚያ በህዝቡ ቅቡልነትን አግኝተው ሁሉም እንደ አባትና መመለሻ አድርጎ ሊቆጥራቸው የሚያስችል ተቀባይነትና ጥንካሬ ሲኖራቸው ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ህዝብን ለማስተማር ከእምነቱ ባፈነገጠ አስተሳሰብ በማጥመቅ ሳይሆን ከእምነቱ ምንጭ በተቀዱ ድንጋጌዎች በመገሰፅ፤ በዘመቻ መልክ ሳይሆን በተጠናና ሁሉን ባማከለ አተገባበር፤ መንግስት ሃይማኖትን ሽፋን አድርጎ በአንዱ እምነት ላይ ብቻ በሚያደርገው ጣልቃ ገብነት ሳይሆን ሁሉም የሃይማኖት ተቋማትና ምዕመኑ በየእምነቶቻቸው ውስጥ ስልት ቀይሰው ልጆቻቸውን ሲያስተምሩ ያጠፋውንም ተገቢውን የእርምት እርምጃ እንዲያገኝ የሚያስችል መንገድ ሲኖራቸው ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ግን በየትኛውም ቦታና ግዜ በማንኛውም አካል የሚፈፀምን ‹የጥፋት፤ የሽብር እና የእልቂት› ተግባራት እንደምናወግዘው ሁሉ ‹የአክራሪነት አስተሳሰብን ለመቀልበስ› በሚል ሰበበ ዜጎችን የእምነት ነፃነት በመንፈግ የመንግስት ባለስልጣናት የሚያሳዩዋቸውን ያልተገሩ የንግግርና የተግባር ጣልቃ ገብነትንም እናወግዛለን፡፡
የሸኽየውን አስተምህሮ እውነተኝነቱን የመሰከሩት ባለስልጣናትን ጨምሮ ሌላ ማንም አካል ፈለጉን የመከተል መብቱ የተጠበቀ መሆኑን የሃገራችን ህገመንግስት ይደነግጋል፡፡ እኛም እናከብረዋለን፡፡ ሆኖም ግን በመንግስት የ‹ጥናት ሰነዶች› የ‹አክራሪ እስልምና› መገለጫዎች ተብለው ፍርደ ገምድል የተበየነባቸው በርካታ እስላማዊ ክንዋኔዎችና ማህበራዊ ትስስሮች ሙስሊሙን ለማሸማቀቅ ማንም እንዳሻው እየተጠቀመበት በመሆኑ ‹የጥናቱን› ባዶ ይዘት እንደምንኮንነው ሁሉ በሸኽየው የተፈበረከውን ‹አዲስ የተጠና ሃይማኖትም› መቃወማችን ህገ መንግስታዊ መብታችን ነው፡፡ ይህንንም ህገመንግስታዊ መብት መጠቀምና በወገኖቻችን መስዋዕትነት የተቋቋሙ የሃይማኖት ተቋሞቻችን ከምንጩ የተቀዳው ነባሩ እስልምና ሳይሆን የዚህ ‹አዲስ የተጠና ሃይማኖት› መሰበኪያ መሆናቸውን መቃወም ‹‹ወሃብያዎች፤ አክራሪዎች፤ ፅንፈኞች፤ ፀረ ሰላሞች›› እና ሌላ ብዙ ብዙ እየተባልን አንዳንዴም ይህን ተከትሎ በታችኛው የአስተዳድር መዋቅር አካባቢ የሚወሰዱ ሚናቸውን ያልለዩ አስተዳደራዊ በደሎች እየተበራከቱ ነውና እነዚህ የማሸማቀቅና የማዋከብ አስተሳሰቦችና ተግባራትን መንግስት በማስቆም የዜጎቹን መብትና ደህንነት ሊያስጠብቅ ይገባዋል እንላለን፡፡
በሌላ በኩል የአስተሳሰቡ ፈላስፋም ሆኑ እስከ አሁን ያሉ የየትኛውም ሃገር ዜጋ የሆኑ ተከታዮቻቸው የሃይማኖት መስመራቸውን ‹‹አህባሽ›› የሚለው መጠሪያቸው የሚታወቅና የሌላው አለም ተከታዮቻቸው ሳይቀሩ በዚህ ስያሜ እንደሚኮሩበትም በይፋ መግለፃቸው በተጨባጭ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን ሌላ ድብቅ አላማ ያለ በሚያስመስል ሁኔታ የአስተምህሮቱን አምላኪዎች ‹‹ሱፊ-ሱኒ›› ተቃዋሚዎቹን ደግሞ ‹‹ወሃብያ፤ አክራሪ….›› እያሉ መከፋፈልና ማዋከብ ለሃገርም ለህዝብም አይበጅምና ይቁም እንላለን፡፡ በተግባር እንደምናየውም የባለስልጣናቱን አይዞህ ባይነት ተንተርሰው በየትኛውም የኢትዮጵያ ታሪክ ያላየነውን የትኛውም ግፈኛ ባለስልጣን በህዝባችን ላይ ያልፈፀመውን ሙስሊሙን የመሰነጣጠቅ እስትራቴጂ ‹‹ሱፊ›› አልያም ‹‹ወሃብያ›› ብለህ ሚናህን ለይተህ ተመዝገብ እየተባሉ ፎርም ማስሞላት መጀመሩ ከዚህም አልፎ የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. ሙስሊም አባላትን ‹‹ወይ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. ን አልያም ወሃብያን ምረጥ›› እያሉ ማሸማቀቅ ተለምዷልና ይህ ሙስሊሙን የማዋከብና የማሸማቀቅ ጥቁር ታሪክ በእንጭጩ መቀጨት ለጋራ ኢትዮጵያችን ይበጃልና ግዜ አይሰጠው እንላለን፡፡

X. ሁሉም ዘመናት ያልተሰሙ የንፁሃን ዜጎች ድምፆች አሏቸው
ታሪክ እንደሚያስተምረን አድማጭ ያገኙ ጩኸቶች ሁሉ ትክክለኛ፤ መፍትሄ ያጡ ብሶቶች ሁሉ ደግሞ መሰረተ ቢስ እንዳይደሉ ነው፡፡ የህዝበ ሙስሊሙ የእምነት ነፃነት ጥሰት ይቁም አቤቱታ ለግዜውም ቢሆን በቂ ምላሽ አለማግኘቱ በጥያቄዎቻችን ሳይሆን ምላሽ መስጠት በሚገባቸው አካላት ላይ ነው እንድናፍር የሚያደርገን፡፡ ለዚህም ትልቅ ማስረጃ መሆን የሚችለው የቅርብ ግዜ ትዝታችን የሆነውና የ1966ቱ መላው የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መሰረታዊ የመብት ይከበርልኝ ጥያቄ ነው፡፡ ምንም እንኳን ወቅቱ የመብት ጥያቄን ሊያውም ሙስሊሙ ህብረተሰብ ለማንሳት ይደፍራል ተብሎ በማይታሰብበት፤ የስልጣን ዙፋኑ ሰማያዊ በሆነ ሹመት የተደላደለ ተደርጎ የሚቆጠር አምባገነን የአፄ ስርዓት በነበረበት ወቅት ለኛ ለሙስሊሞች የጨለማውን ዘመን የማስቆምና ያለማስቆም የህልውና ጥያቄዎችን ያነገበ ታሪካዊ ክስተት ተመዝግቧል፡፡ በዚያን ወቅት የተነሱት ጥያቄዎች ካላቸው እጅግ ወሳኝ ይዘትና ስርዓቱ ከነበረበት እጅግ የገዘፈ ፀረ ኢስላም አስተሳሰብ አንፃር ሲቃኝ የማይጠበቅ ግን ደግሞ የእኛ የሙስሊሞችን ታሪክ የቀየረ፤ ‹በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሙስሊሞች› ከመባል ‹ሙስሊም ኢትዮጵያውያን› ያስባለን፤ በወሳኝ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይም ቀጥተኛ ተሳታፊና ተጠቃሚ የመሆን መብትን ያጎናፀፈ ነበረ፡፡ የደርግ ስርዓትም እንደ አቋም ፀረ ሁሉም ሃይማኖት ቢሆንም ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ግን ለዘመናት የተነፈጉትን ከሌሎች አቻ ሃይማኖቶች እኩል መቆጠራቸውን የሚያረጋግጡ አያሌ ለውጦችን ያገኙበት ሁኔታ ነበረ፡፡ ዛሬ ዛሬ የእምነት ነፃነት ዳግም ጥያቄ ለመሆን በማይችልበት መልኩ መልስ አግኝቷል ተብሎ በሰፊው በሚቀነቀንበት የኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. መንግስት ዘመን እጅግ ቀላል ግን ደግሞ ወቅታዊ የሆኑ የመብት ጥያቄዎቻችንን የሚያደምጥና በቀናነት አጢኖ አጥጋቢ ምላሽ የሚሰጥ አካል አልተገኘም፡፡ ሃገራችን በብዙ መልኩ ወደፊት ስትራመድ የሙስሊሞችን የመብት ጥሰት ለማስቆም ወሳኝ አመራር መታጣቱ ግን ግዜውን ከ 38 አመታት በፊት በያዝነው ሳምንት ላይ ሙስሊሞች ላነሳነው የመብት ጥያቄ የወቅቱ አምባገነን መሪዎች የሰጡንን ጆሮ ያህል እንኳን ማጣታችን ፍትህ በስርዓቱ አተረጓጎም ለሙስሊሞች ሲሆን ይለይ ይሆን ብለን እንድንጠራጠር አስገድዶናል፡፡
ጉዳዩን በቀና አእምሮ ስናስበው ደግሞ ‹አስቀድሞ የበሰለ ፍሬ አስቀድሞ ይቆረጣል› የሚለው ብሂል እውነት ነውና ይህን መሰሉ ሙስሊሙን የማሸማቀቅና የማዋከብ ሴራ ላይደገም ይቀበር ዘንድ ዋስትና የሚያስፈልገው መልስ ስለሚፈለግ ለዚህ የሚሆን ትዕግስትና ፅናት ህዝበ ሙስሊሙ የተማረበትም ታሪካዊ ሃገራዊ አጋጣሚ ነው፡፡ በትጥቅ ትግል ወቅት ያገኘውን የአላማ ፅናት ያለውን ፋይዳ የሚያስረዳ ትምህርት ያስተማረን ኢህአዴግ በሰላማዊ የመብት ጥሰት ይቁም ጥያቄ ላይ ይህ መርህ አይሰራም ብሎ እንደማይሞግተን እናምናለን፡፡ በመሆኑም ጥያቄዎቻችን ተገቢውን ምላሽ አግኝተው ደማቅ ታሪክ እንዲሆን ስንመኝ ይህ ሳይሆን ቀርቶ የመብት ጥያቄዎቹ እና ጠያቂዎቹ ላይ የተፈጠረው የማዋከብና የማሸማቀቅ ተግባር ጠያቄዎቹን በስልትም ሆነ በሃይል ማስቆም ቢሳካለት እንኳን እነዚህ ነፃና ፍትሃዊ ጥያቄዎች ግን በኢ.ህ.አ.ዴ.ግ. ዘመን ሰሚ ያጡ የህዝበ ሙስሊሙ ፍትሃዊ ድምፆች ተብለው በታሪክ መዘገባቸው አይቀርም፡፡

XI. ዛሬም ለጥያቄዎቻችን በቂና ግልፅ ምላሽ ይሰጠን ስንል እንጠይቃለን
ባሳለፍናቸው የመብት ጥያቄ ሂደቶች የጥያቄዎቻችንን ይዘትና ፍትሃዊነት ለማስረዳት ያልፈነቀልነው ድንጋይ አልነበረም፡፡ ለመንግስት አካላት እና ለሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄዎቻችን ምን እንደሆኑ፤ ምላሽ አገኙ የሚባሉትስ መቼ ነው የሚለውን በማያሻማ አገላለፅ በማስረዳታችን ሁሉም ማለት በምንችልበት ደረጃ የየትኛውም እምነት ተከታይ ወገኖቻችንን ‹ጥያቄዎቻችሁ የመብት ጥያቄዎች ናቸው የመንግስትን ምላሽ ይሻሉ› የሚል አኩሪ የህዝብ ለህዝብ አጋርነት አፀፋ ለማግኘት ችለናል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ሁሉም ማለት ባንችልም በሂደቱ ውስጥ እጃቸው ያለበት አብዛኞቹ ባለስልጣናት ለህዝብ ከህዝብ ይልቅ የሚያውቁለት እነርሱ እነደሆኑ የሚያስመስል፤ ሚሊዮኖች የሆኑ የመብት ጠያቂዎችን የጥቂት ፅንፈኞች ጀሌዎች አስመስሎ በማወጅ ብዙሃንን ያላዋቂ አድርጎ የመሳል ችግር፤ የመብት ጠያቂውን ህዝበ ሙስሊም እምታቸውን የታደጉ መስሏቸው የተታለሉ ናቸው የሚል ሙስሊሙን ለእምነቱ ባዳ አድርጎ የማቅረብ አጓጉል አካሄድ ተስተውለዋል፡፡ አልፎ አልፎም የጥያቄዎቹን ይዘትና የአቀራረብ ስልታቸውን በግድ በመጠምዘዝ አቅጣጫ ለማሳት ሲሞከርም አስተውለናል፡፡ እነዚህ ሁላ ነገሮች ግን የተነሳበትን ለሚያውቀው ህዝበ ሙስሊም መድረሻውን አያስጠፉትምና መቼም አይሳካም፡፡ ጥያቄዎቻችን ለማንም የማይከብዱ እጅግ በጣም ቀላልና ግልፅ ቢሆኑም ዛሬም ደግመን እንደሚከተለው አስቀምጠናቸዋል፡፡
በህዝበ ሙስሊሙ ይሁንታ ባላገኙና ባልተመረጡ በጓሮ በር ገብተው የሙስሊሙን ሁለንተናዊ ስብዕና በመግፈፍና የመጅሊስን ተቋም በብልሹ አሰራር እየመዘበሩ ያሉትን የመጅሊስ አመራሮች ሙሉ ለሙሉ ተወግደው ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለሀይማኖቴም ለሃገሬም ይጠቅመኛል የሚለውን መሪ በየመስጂዱ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት፤ ህዝብ በተስማማበት የምርጫ ስረዓት፤ አስመራጭ፤ ታዛቢ፤ አስፈጻሚ ነጻ፤ ግልጽና ፍትሀዊ በሆነ መልኩ እንዲካሔድ ይፈልጋል፡፡
በመጅሊሰ ፊታውራሪነትና ባንዳንድ የመንግስት አካላት ድጋፍ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ በግዴታ እየተጫነ ያለውን የአህባሽ አስተምህሮና አስተሳሰብ ሙሉ ለሙሉ እንዲቆም፡፡ አህባሽ እንደማንኛውም የእምነት ተቋም ራሱን ችሎ መንቀሳሰቀስ እንደሚችል በህገ መንግስቱ በግልፅ የተቀመጠ እንደመሆኑ በሙስሊሙ ተቋማት ላይ ግን ሙሉ ለሙሉ እጁን እንዲያነሳ እንጠይቃለን፡፡

አላሁ አክበር

[A1]የጋዜጣውን ስምና ቀን ማግኘት አልተቻለም፤ እናም አስፈላጊ ከሆነ በቀይ የተቀለመው መውጣት ይችላል

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on April 6, 2013 in Uncategorized

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: