RSS

በኢትዮጵያ ያለውን የሙስሊሞችመብት ጥያቄን በመደገፍ እንዲሁም የአብደላ ሃረሪ (አህበሽ) አስተምህሮን በመቃወም በሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ የተጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት መጠናቀቁ ተገለጸ

06 Apr

በኢትዮጵያ ያለውን የሙስሊሞችመብት ጥያቄን በመደገፍ እንዲሁም የአብደላ ሃረሪ (አህበሽ) አስተምህሮን በመቃወም በሚኒያፖሊስ ሚኒሶታ የተጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ ባለ 7 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት መጠናቀቁ ተገለጸ።
በሚኒሶታ የሚገኙት ቶፊውፊቅ፣ ኢቅራዕና ተውሂድ እስላማዊ ማዕከላት በጠሩት በዚህ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ከኢትዮጵያ በቀጥታ በስካይፒ በሕዝብ የሚደገፉት ሼህ አህመድ ጀበል በስካይፒ በኢትዮጵያ ያለውን የሙስሊሞች ሁኔታና የትግሉን እንቅስቃሴ አስረድተዋል።
በሚኒሶታ ታዋቂ የሆኑት ሼህ ከማል አህመዲን ባደረረጉት ሰፊ ንግግር ላይ የመለስ ዜናዊ መንግስት የ እስልምና ሃይማኖትን በመክፈል አንዱን በመደገፍ አንዱን በማራቅ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ጥሩ አይደለም ሲሉ ተችተዋል። እርሳቸው እየተናገሩ ሳለም ከዚህ ቀደም ሼህ የሱፍ “አቶ መለስ የአህበሽ አስተምህሮ ለኢትዮጵያ ሙስሊም ጥሩ ነው የሚሉ ከሆነ እርሳቸው ለምን እምነቱን አይቀበሉትም?”ሲሉ የተናገሩት ተጠቅሶ ሕዝበ ሙስሊሙን ፈገግ አሰኝተዋል።
“እስልምና በሂሳብ ተሰልቶ የሚታመን ወይም እንዲህ ቢሆን እንዲህ ይሆናል ተብሎ የሚታመን እምነት አይደለም” ያሉት ሼህ ከማል በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሙስሊሞች ሃይማኖታቸው በመነካቱ የተነሳና የመንግስትን በ እምነት ውስጥ ያስገባውን ጣልቃ ገብነት ለመቃወም አደባባይ ወጥተው መብታቸውን ለማስከበር ላለፉት 3 እና 4 ወራት ያደረጉትን ትግል አድንቀው እዚህ በሚኒሶታ የምንገኝ የሙስሊም ማህበረሰብም ከጎናቸው ነን ብለዋል። “ማንም ሰው መብቱ ሲነካ ተነስቶ መብቱን የመጠየቅ ግዴታ እንዳለበት ያሰመሩበት ሼህ ከማል “በሕዝብ ያልተመረጠ መጅሊስ ሙስሊሙን መምራት የለበትም” ብለዋል።
በሕዝብ ያልተመረጠና በመንግስት የተቀመጠ መጅሊስ የመንግስትን የፖለቲካ ሥራ እንጂ የሃይማኖት ሥራን እንደማይሰራ አበክረው የገለጹት ሼሁ፤ የሙስሊሞቹ የመብት ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ በሕዝብ የተመረጡ የመጅሊስ አባላት እንዲቀመጡ ጠይቀዋል።
በንግግራቸው መጨረሻ ላይም ሼሁ “በተለይ የኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን የሙስሊም ወንድሞቹ መብቱን ለመጠየቅ ሲነሳ ከጎን በመቆም መብታቸው ይከበርላቸው በማለታቸውና ድጋፋቸውን በመስጠታቸው እናመሰግናለን” ብለዋል።
በስብሰባው ላይ የተለያዩ በሚኒሶታ የሚገኙ የ እስልምና የሃይማኖት አባቶች ንግግር ያደረጉ ሲሆን በአወሊያ ተጀምሮ በመላው ሃገሪቱ እየተስፋፋ ያለውን ትግል እንደሚደግፉ፤ ተናግረዋል። በመጨረሻም ይህ ሕዝባዊ ኮንፈረንስ ባለ7 ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል። ሙሉ መግለጫው የሚከለተለው ነው።
ሚያዝያ 27/2004 (ሜይ 5/2012 )
የቶፊውፊቅ፣ የኢቅራዕናተውሂድ እስላማዊ ማዕከላት ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላይ ባሁኑ ወቅት እየደረሰ ያለውን የመብት ጥሰት በመቃወም የተሰጠ የአቋም መግለጫ
ምስጋና ለአላህ ይግባው፤ ሰላምና ሰላት ለታላቁና ለተወዳጁ ነብያችን ሙሃመድ (ሰ.አ.ወ) ይደረሳቸው።
ይህ በአሜሪካን ሃገር በሚኒሶታና አካባቢው በምንገኝ የተውፊክ፣ ኢቅራዕ እና ተውሂድ እስላማዊ ማእከላት ስር በታቀፍን ሙስሊሞች በጋራ በመወያየትና የሃገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ በጥልቀት ከመረመርን በኋላ በዛሬው እለት ሜይ 5/2012 ባደረግነው ስብሰባ ላይ የወጣ የአቋም መግለጫ ነው።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሙስሊም ሕብረተሰብ ላይ በየ ዕለቱ የመብት ጥሰት፣እየተባባሰ መምጣቱ ለሁሉም ወገን ግልጽ ነው። ከጥቂት ወራት በፊት የአወሊያ እስላማዊ ኮሌጅን ማዕከል አድርጎ የተጀመረው የሕዝበ ሙስሊሙ የመብት ጥያቄ ወደ አላስፈላጊ ግጭት እንዲያመራ ሆን ተብሎ እየተደረገ መሆኑን ከሰሞኑ የሚታዩት አሳዛኝ ክስተቶች እያረጋገጡልንነው። የሃገሪቱ ህገ መንግስት የሰጠውን የዜጎች የ እምነት ነጻነት መብት በከፍተኛደረጃ እየተጣሰ መሆኑን ከተገነዘብን ሰንብተናል። አልፎ ተርፎም ሙስሊሙ ሊከተለው የሚገባውን የ እምነት መስመር መምረጥና ሃይማኖታዊ ፈትዋ (ብይን) በመንግስት ባለስልጣናት መሰጠት ሁሉ ተጀምሯል። በተጨማሪም ኤፕሪል 17/2012 የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚ/ር በተወካዮች ምክር ቤት ሙስሊሙን አስመልክተው በሰጡት የተዛባ መግለጫ እጅጉን አዝነናል።መንግስት በሙስሊሙ ማህበረሰብ ለተነሳው ቀጥተኛውና ግልጽ የመብት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ አለመሆኑን ጭምር አመላክቶናል። በመሆኑምበዛሬው ዕለት ባደረግነው ሕዝባዊ ስብሰባ ከዚህ በታች በዝርዝር የተቀመጡት አቋሞች ላይ መድረሳችንን እንገልጻለን፦
1ኛ. አወሊያን ማዕከል አድርጎ የተቋቋመውን መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ከልብ የምንደግፍ መሆኑን አበክረን እናስታውቃለን። ኮሚቴው በሕዝብ ስም ያቀረባቸውን ሕጋዊና ፍትሃዊ የመብት ጥያቄዎች በየምክንያቱ ማዘግየትና ተዛማጅነት የሌላቸውን ምክንያቶች መደርደር አግባብ አለመሆኑን እየተቃወምን ተገቢው ምላሽ በአስቸኳይ እንዲሰጣቸው እንጠይቃለን።
2ኛ. በአሁኑ ወቅት የሕዝብ ውክልና የሌለው መጅሊስ አመራር በአፋጣኝ ከስልጣኑ ተወግዶ በምትኩ በገለልተኛ አስመራጭ አካልና በነጻ ምርጫ መስጊዶችን ማዕከል በማድረግ አዲስ እና ሕዝባዊ ውክልና ባለው አመራር እንዲተካ እንጠይቃለን።
3ኛ. መንግስትና አንዳንድ የመንግስት አካላት በሕዝበ ሙስሊሙ ተቀባይነት ያላገኘውንና በበርካታ ዓለም አቀፍ ምሁራን ከእስልምምና አስተምህሮት ማፈንገጡ የተነገረለትን የአብደላ ሀረሪን(አህበሽ) ያስተሳሰብ መስመር በሕዝቡ ላይ በግዳጅ የመጫኑ ተግባት በአስቸኳይ እንዲገታ አጥብቀን እንጠይቃለን።
4ኛ. የዓለም ሰላም ወዳድ ኃይሎች፣ መንግስታትና የሰብአዊ መብት ጥበቃ ተቋማት ይህን በሃገራችን ሙስሊም ማህበረሰብ ላይ እየደረሰ ያለውን ገደብ የለሽ የመብት ጥሰት ተገንዝበው ከጎናችን እንዲቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
5ኛ. በሃገራችን የሚገኙ የሁሉም ሃይማኖት ተከታይ ዜጎች፤ የሃይማኖት ልዩነት ሳይገታቸው ለሰብዓዊ መብት መከበርና ለዕምነት ነጻነት በጋራ እንዲቆሙ የበኩላችንን ጥሪ እናቀርባለን። እርስ በእርስ የመከባበርና የመቻቻል ባህላችንንይበልጥ ተጠናክሮ እንዲጎለብት የሁሉም ወገን ጥረት ከፍ እንዲል ለማስገንዘብ እንወዳለን።
6ኛ. በዓለም ዙሪያ የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የገጠመንን የጋራችግር፤ በጋራ መታገል ውጤታማ ስለሚያደርገን አንድነታችንን አጠናክረን፤ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንድናደርግ ጥሪያችንን እናቀርባለን።
7ኛ. በቅርቡ በአርሲ ዞን በገደብ አሳሳ ውስጥ በንጹሃን ሙስሊም ወገኖቻችን ላይ በመንግስት የጸጥታ ኃይላት የደረሰውን አሰቃቂ የግድያ እርምጃ፣ እስራትና እንግልት አምርረን እናወግዛለን። የደረሰው ጥፋት በገለልተኛ አካል ተጣርቶ አጥፊዎቹ በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ እንጠይቃለን። በአሁኑ ወቅት በእስር ቤት በመንገላታት ላይ ያሉ ወገኖቻችንም ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ አጥብቀን እንጠይቃለን። ለሟች ቤተሰቦችም አላህ መጽናናቱን እንዲሰጣቸውና በሞት የተለዩን ወገኖቻችንን ጀነት እንዲለግሳቸው እንጸልያለን።
*. ኢስላም የሰላም ሃይማኖት ነው!
*. የእምነት መብታችን በትግላችን ይከበራል!
*. አንድነታችን ሁሌም ኃይላችን ነው!
*. ከአወሊያ አስተባባሪ ኮሚቴ ጋር ዘወትር በጽናት እንቆማለን!
አሰላሙ አለይኩም ወረህመቱላሂ ወበረካቱ።
የቶፊውፊቅ፣ የኢቅራዕና ተውሂድ እስላማዊ ማዕከላት ማህበረሰብ
ሜይ 5/2012 ሚኒያፖሊስ፤ ሚኒሶታ::

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on April 6, 2013 in Uncategorized

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: