RSS

አዲሱ አቅጣጫ

05 Apr

አዲሱ አቅጣጫ

የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ሐይማኖታዊ የመብት ጥያቄ ሌላ መልክ እንዲይዝ እየተደረገ ያለው ጥረት ቀጥሏል፡፡ የዚህ ዕቅድ ጥንስስ አሀዱ ብሎ መጀመር ጥቂትም ቢሆን የሰነበተ ቢሆንም “ካለፈው ግድፈት ” ትምህርት በመውሰድ በተጠናከረ አቀራረብ እንዲተገበር እየተሞከረ ይገኛል፡፡ የሙስሊሞች የህልውና እና የመብት ጥያቄ የትኛውንም ጀመዓ በተናጠል የወከለ ሳይሆን ሁሉንም የጀመዓ ክፍሎች በአንድ ላይ ያጠቃለለ መሆኑ በሙስሊሙ ዘንድ እጅጉን እየታወቀ አንዳንድ የመንግስት አካላት እያካሄዱት ባለው ተንኮል የተሞላበት እንቅስቃሴ ወቅታዊው የሙስሊሞች እንቅስቃሴን በ “ወሀቢዮች” እና በ “ሱፊዮች” መካከል የሚደረግ ግብ ግብ እንዲሆን ለማድረግ ሌት ተቀን በመጣር ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህ አካሄዳቸው የህዝብ ዕውቅና ሳይኖራቸው የሙስሊሞች መንፈሳዊ ተቋም የሆነውን ድርጅት በተቆጣጠሩት አካላትና ጥቂት አጋሮቻቸው ዘንድ ፍፁም ተቀባይነት በማግኘቱና ስልጣናቸውን ለማራዘም ያግዛቸው ዘንድ ራሳቸውን “ሱፍያ” ብለው በመሰየም ትግሉ በ “ወሀቢያ” እና “በሱፍያ” መካከል እንደሆነ አምነው ተቀብለው ሌሎችም ይህንኑ አስተሳሰብ እንዲከተሉ መንገድ ጀምረዋል፡፡
የዚሁ ዕቅድ አካል ሆኖ የተወሰደው ስራ በተለያዩ መድረኮች እየተተገበረ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በትላንትናው ዕለት ማለትም ቅዳሜ ሚያዚያ 13/ 2004 ከ 80 የሚበልጡና ከየክልሉ የተጠሩ የመጅሊስ አካላት ጦር ኃይሎች በሚገኘው በፌዴራል መጅሊስ ቅጥር ጊቢ ስብሰባ ተካሂዷል፡፡ በስብሰባው እንዲካፈሉ ጥሪ የተደረገላቸው ግለሰቦች ማንነት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች መውሊድን የማክበር እና የማስከበር ልምድ ያላቸው መሆኑ ሲታወቅ እነኚህኑ ሰዎች በዋናነት መጥራት ያስፈለገበትም ምክንያት የመውሊድ አከባበር አንዱና ዋነኛ ትኩስ የስውር አጀንዳ ማስፈፀሚያ መሣሪያ ይሆናል ተብሎ በመታመኑ ነው፡፡
በዕለቱ ስብሰባ ላይ አቶ አህመዲን አብዱላሂ፣ ሀጂ ጠሃ እና የ ዑለማዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ለተሰብሳቢው ንግግር አድርገዋል፡፡
አህመዲን አብዱላሂ ባደረገው ንግግር ጠቅላይ ምክር ቤቱ እየሰጠ የቆየው ስልጠና ትክክለኛውን የአህለ ሱና ወል ጀመዓ አስተምህሮት እንደሆነና “ወሀቢያዎች” እያጥላሉት ያለው ይህንኑ አስተምህሮት ነው ብሏል፡፡ እናንተ ሱፊዮች ተጠናክራችሁ ከጎናችን ከሆናችሁ “ወሀቢያዎችን” እናሸንፋቸዋለን በማለት ጠንካራ የሚባል ቅስቀሳ አድርጓል፡፡ ከንግግሩ ማጠቃለያዎች መካከልም ተሰብሳቢዎች ወደየመጡበት ተመልሰው መውሊድን በማክበር ሽፋን “ሱፍያዎችን” በማደራጀት “ወሀቢያዎችን” መታገል እንደሚገባቸው ለዚህም መጅሊስና መንግስት ከጎናቸው መሆኑን አረጋግጦላቸዋል፡፡
ሀጂ ጠሃ ባደረገው ንግግር “ትግሉ” በ “ወሀቢያ” እና “ሱፍያ” መካከል መሆኑን፣ “ወሀቢያ” አመፅና ረብሻ በየመስጂዱና በየቦታው እያነሱ መሆናቸውን እና “ወሀቢያዎች” መስጂዶቻችንን ደፈሩ ያለ ሲሆን ይህ የ “ወሀቢያ” ሩጫ እኛን “ሱፊያዎችን” ለማጥፋት በመሆኑ ተደራጅተንና ተጠናክረን በምንችለው አቅም መዋጋት አለብን በማለት ቁጣ በቀላቀለበት እና ስሜት በሚያነሳሳ መልክ ተሰብሳቢውን ቀስቅሷል፡፡
የፕፌሰርነት ማዕረግ እንዳላቸው የሚነገርላቸው የዑለማ ምክር ቤቱ ፕሬዝዳንትም ስለ “ሱፍያ” ምንነት ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡
ተሰብሳቢዎቹ “ይኸው እኛ ሄደን አይተን መጣን መጅሊስ እየሰራ ያለው ስራ ምንም ነውር የለበትም፣ አህባሽ ምናምን እየተባለ የሚወራው የ “ወሀቢያዎች” ውሸት እንጂ እኛ በወሰድነው ስልጠና ምንም አዲስ ነገር አላገኘንበትም” እንዲሉ የተፈለገ በመሆኑ በስብሰባው ላይ ከዚህ ቀደም የነበረው ዓይነት አስተምህሮትና ዘዴው በውል አልቀረበም፡፡ ይህም ተሰብሳቢዎችን ላለማስበርገግና በሚሄዱበት ቦታ በሀሰት እንዲመሰክሩ ለማድረግ በማሰብ እንደሆና ምንጮች አስረድተዋል፡፡
የዕለቱ ስብሰባ ሃይለ ቃልና ስሜት የሚያነቃቃ ንግግር የታጨቀበት ሲሆን “ እናንተ ሱፊያዎች ሆይ! ተነሱ፣ ይህ የሞት ሽረት ትግል ነው” የሚሉ ቃላቶች ከመድረኩ ሲወረወሩ መዋላቸውን ለማወቅ የተቻለ ሲሆን “ወሀቢያ” አሁን እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ የሚያወግዝ፣ ትግሉም የሚቀጥል መሆኑን የሚያትት እና ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ነጥቦች ያካተተ ባለ ሰባት (7) ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ስብሰባው ተጠናቋል፡፡
ስብሰባው በመንግስትና በግሉ ሚዲያ ሽፋን እንዲያገኝ በማሰብ ከ30 (ሠላሣ) በላይ ለሚሆኑ የሚዲያ ባለሙያዎች ጥሪ የተደረገ ሲሆን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትም በቦታው በመገኘት ዘግቧል ፡፡ ሆኖም የፕሮግራም አዘጋጁ ፕሮግራሙን ለአየር ስርጭት እንዲበቃ መሰናዶውን ቢጨርስም የበላይ አለቆች ዝግጅቱ በሀይለ ቃል የታጨቀ በመሆኑ ምክንያት ፕሮግራሙ ቢተላለፍ ህዝቡን ይቀሰቅስብናል ሲሉ በመስጋታቸው እስካሁን እንዳይተላለፍ መታገዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on April 5, 2013 in Uncategorized

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: