RSS

ጠንካራ መጅሊስ የምንፈልገው ለምንድነው?

16 Feb

ይህ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ሙስሊሞች በአንድ በኩል እና በመጅሊስ አመራሮችና አንዳንድ ፖለቲከኖች በሌላ በኩል ሆነው እየተካረረ የመጣው ግጭት አዲስ አይደለም፡፡ የኢስላምንና ሙስሊሙን ጥንካሬ የሚወዱ በአንድ ወገን፤ የኢስላምንና ሙስሊሙን መዳከም ከተቻለ መክሰም የሚሹ በተቃራኒ ወገን ተሰልፈው የሚያካሄዱት ትግል ከመጀመሪያው ሰው እና ነብይ አደም(ዐ.ሰ) ጀምሮ የነበረ ነው፡፡

ከነብዩላህ አደም (ዐ.ሰ) ጀምሮ እስከ ነብዩ ሙሐመድ (ሶ.ዐ.ወ) ያሉት ነብያት፤ የነብያቱ ወራሾች የሆኑት ዓሊሞች እነ ሸህ ዳና፣ ሸህ ዒሳ ቃጥባሬ፣ ሸህ ሰይድ ሙሐመድ ሳዲቅ፣ ሐጅ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ፣ ሐጅ ሙሐመድ ራፊዕ፣ የወለኔው ሸህ፣ የሾንኬው ሸህ፣ ሸህ አባዲር እና ሌሎች በሕይወት የሌሉ ሆነ ያሉ ዓሊሞች፣ ጻድቃኖች መልካም አማኞች በሙሉ (የአላህ እዝነትና ርህራሄ በሁሉም ላይ ይሁን) ለኢስላምና ሙስሊሙ ጥንካሬ ብርታት እና እድገት ለፍተዋል፣ ጥረዋል፣ ሕይወታቸውን ገብረዋል፡፡

ከነዚህኛዎቹ የአላህ ወዳጆች በተቃራኒ ከኢብሊስ ጀምሮ እነ ፊርዓዎን፣ ነምሩድ፣ ቃሩን፣ አብረሃ፣ አቡጃህል፣ አቡለሃብ፣ የአይሁድ አመራሮች፣ ሙናፊቆች እንዲሁም መሰሪ ፖለቲከኞች (ሙስሊም ሆኑ አልሆኑ) በአንድ ላይ ኢስላምንና ሙስሊሙን ለማዳከም ሌት ተቀን ሲያውጠነጥኑ፣ ተንኮል ሲሸርቡ፣ ሲገድሉ ሲያስገድሉ፣ ሙስሊሙን ለመከፋፋል ከጀርባው ሲወጉና ሲያስወጉ የኖሩ ናቸው፡፡

በአወሊያ ይኸው ለስድስተኛ ሳምንት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች እንዲሁም በተለያዩ ምክንያቶች በቦታው ሳይገኙ የቀሩ በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ ያለው ምኞት በነቢያቱ፣ በዓሊሞች፣ በጻድቃኖችና በሰማዕቶች ልብ ውስጥ የነበረው የኢስላምና ሙስሊሞች የመጠናከር ዓላማና ምኞት ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ እነዚህን ከአደም ጀምሮ የነበሩ በአሁኑ ወቅት በየትኛውም የዓለማችን ጥጋ ጥግ ያሉ ቀናኢ አማኞች የሚደግፉትን የኢስላምና ሙስሊሙ መጠናከር የዘመናት ተልዕኮ ለማሳካት ይዘው የተነሱትን በአወሊያ የተሰባሰቡ ሙስሊሞችን ለማስመታት፣ ‹‹አክራሪ ናቸው››፣ ‹‹አሸባሪ ናቸው›› እያሉ የሚያስወሩ፣ ማስታወቂያዎችንና ደብዳቤዎችን የሚለጥፉና የሚልኩት የመጅሊስ አመራሮችና አንዳንድ ፖለቲከኞች የኢስላምንና ሙስሊሙን መዳከም ብሎም መጥፋት የሚፈልጉ የሙናፊቆችን፣ አብርሃን፣ ፊርዓውንና ሸይጣንን ዓላማ የያዙ ናቸው፡፡

እነዚህ ሰዎች የእነዚህን ከይሲዎች ዓላማ ባይዙ ኖሮ የግጭቱ መልክ እንዲህ አይሆንም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላይ ጦርነት አያውጁምም፡፡ የኢስላምንና ሙስሊሞችን ጥንካሬ በሚፈልጉ ስራዬን ሳይሉ፣ የፀሐይ ሐሩር ሳይበግራቸው የኢስላምንና ሙስሊሞችን መጠናከር ፈልገው በተሰባሰቡት ላይ ‹‹አሸባሪ ናቸው!›› ብለው ጣቶቻቸው ባልቀሰሩ፣ ምላሳቸውን ከላቃቸው ባላላቀቁ፡፡ እነዚህ ሰዎች የኢስላምንና ሙስሊሞች መጠናከር ቢፈልጉ ኖሮ የመጅሊስ ይጠናከር ጥያቄዎች ካነሱ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጎን በቆሙ ነበር፡፡ መጅሊስ በተቋም ደረጃ መያድ (NGO) ሆኖ እንዲቀር የኢስላምንና ሙስሊሞች መዳከም ከሚሹት ጎን ባልተሰለፉ፣ የእነሱንም አጀንዳ ለማስፈጸም ባልተጉ፣ ባልተንቶሰቶሱና ባልቀለሉ ነበር፡፡

ጠንካራ መጅሊስ የምንፈልገው ለምንድነው? በአሁኑ ወቅት ያለው መጅሊስ ከመቼውም ጊዜ በከፋ ደካማ እንደሆነ ማንም የሚጠፋው አይደለም፡፡ ይህን እንኳን ሙስሊሙ ጠላቶቻችንም ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ለዚህም ነው ሌት ተቀን እየተዋጉን ያሉት፡፡

የመጅሊሱ ደካማ ጎኖች የትየሌለ እንደሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም የሁሉም ድክመቶች መንስኤዎች ግን ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው መጅሊስ አወቃቀሩ ደካማ ነው፡፡ መሰረቱ፣ ማገሩ፣ ምሶሶው፤ ግድግዳዎቹና ጣሪያዎቹ በሙሉ መያድ (NGO) ወይም ግብረሰናይ ድርጅት መዋቅር ስለሆኑ የአሸዋ ላይ ቤት በሉት የሸረሪት ድር ይስማማዋል፡፡ በቀላሉ ለጥቃት፣ ለተፅዕኖና ለማፍረስም ጭምር የተጋለጠ ነው፡፡ ሁለተኛው ችግር መሪዎቻችንን አለመምረጥ ነው፡፡ ከየት ይምጡ ማን ያምጣቸው የማናውቃቸው ሰዎች አይምሩን፡፡ መጅሊስ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ቀልብ ነው፡፡ ይህ ቀልብ ከተስተካከለ ሙስሊሙ ይስተካከላል፡፡ ይህ ቀልብ ከተበላሸ ሙስሊሙ በሙሉ ይበላሻል፡፡ ስለዚህ በቀልባችን ላይ አዛዥ ናዛዥ መሆን ያለብን ማንም ሳይሆን የኢትዮጵያ ሙስሊም ነው፡፡ የዕድገታችንም ሆኖ ውድቀታችን ዕጣ ፈንታ ለኛ ሊሰጠን ይገባል፡፡

እነዚህን ሁለት መሠረታዊ የድክመቶች ሁሉ መንስኤዎችን ስንገለብጣቸው መጅሊስ ጠንካራ ይሆናል፡፡ ማለትም መጅሊስ በመያድ ወይም ግብረ ሰናይ ድርጅታዊ መዋቅር ሳይሆን በቻርተር ሲቋቋም፣ ሁለት መሪዎቻችንን ስንመርጥ ኢስላምና ሙስሊሞች ይጠናከራሉ፡፡ ይሄኔ የነሙፍቲህ ዳውድ፣ የነ ሸህ ዳና፣ ሸህ ጫሊ፣ ሸህ ጦልሃ ጃዕፋር፣ ሸህ ዒሳ ቃጥባሬ፣ የወለኔው ሸህ፣ የሸህ አባድር፣ የሸንኬው ሸህ፣ የአልከሰዬ ሸህ፣ የአብረሄት ሸህ፣ ሐጅ ሙሐመድ ሳኒ ሐቢብ፣ ሸህ ሰይድ ሙሐመድ ሳዲቅ፣ ሐጅ ሙሐመድ ራፊዕ ህልም ዕውን ይሆናል፡፡ የዘመናት ምኞታቸው ይሳካል፡፡ ስለሆነም፤ መጅሊሱ ጠንካራ እንዲሆን የምንፈልገው የሸኾቻችን ህልም፣ ትግልና ምኞት እውን ለማድረግ ነው፡፡ ሸኾቻችን ከኢስላምና ሙስሊሞች ጥንካሬ ውጪ ሌላ ምኞት አልነበራቸውም፡፡ ሌት ተቀን የለፉት፣ በረሃ ለበረሃ የተንከራቱት፣ አቀበት ቁልቁለቱን የወጡት የወረዱት፣ አላህን አጥብቀው ሲለምኑት የነበረው ለዚሁ ህልማቸው ነበር፡፡

እስቲ የእኛን እናትና አባቶቻችንን ፊቶች የሞሉን መስመሮች፣ የተሰበሩ አንገቶቻቸውን፣ እንባ አዝለው የፈዘዙ ዐይኖቻቸውን እንመልከት፣ የእነርሱን አባቶችና እናቶች እንዲሁም አያት ቅድመ አያቶች ታሪክ ሲነገር አድምጡ፣ አንብቡ፡፡ በየትምህርት ቤቱና ዩኒቨርሲቲው ያሉትን ወንድሞችንና እህቶቻችን ታሪኮች አድምጡ፡፡ ሁሉም የሚነግሩን አንድ ነገር ብቻ ነው-በኢስላምና በሙስሊምነታቸው ምክንያት ተዋርደዋል፣ ክብራቸው ተገፏል፡፡ ይህ እጅግ በሚያሳዝን አኳኋን እስካሁን ድረስ የዘለቀ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች እውነታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን አገራቸው እንዳልሆነች ያህል ባይተዋርነት ይሰማቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ እንዲህ አይነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርጉን ሰዎች፣ ባለስልጣናትና ቢኖክራቶች ሱፊይ ብንሆን ‹‹ወሃቢያ›› ደንታ የላቸውም፡፡ ሁላችንም በነርሱ ፊት ሙስሊሞች ነን፡፡ ይህ ውርደት የሚደርስብን ኢስላምን የተቀበለን ሙስሊሞች ስለሆንን ብቻ ነው! እንዴትም አድርጋችሁ በአሁኑ ወቅት ያለንበትን ነባራዊ ሁኔታ ሆነ ታሪካችንን መለስ ብለን አይተን ብናጤነው ከዚህ ውጪ ማብራሪያ ልናገኝለት አንችልም፡፡ ብቸኛው የመጠናከሪያ መንገድ የሆነው መጅሊስ ተዳከሞ እንዲቀር ያለሳለሰ ጥረት የሚያደርጉት ለዚሁ ነው፡፡ በአገራችን ቦታችን ዝቅተኛ እንደሆነ፣ መቼውንም እኩል እንደማንሆን እያስገነዘቡን ነው፡፡ በተለያዩ ቃላት እየሸነገሉን ባሪያ ሲጠግብ አናት ላይ ይወጣል እንደሚባለው እስካሁን ያገኛችሁትን ውበት በቂ ነው፤ ከዚህ በላይ ምን ትፈልጋላችሁ እያሉን ተዋርደን እንድንቀር ነው ፍላጎታቸው፡፡ መጅሊስ ጠንካራ እንዲሆን የምንፈልገው ሌላው ምክንያት ለዚህ ነው፡፡ ይህ የዘመናት ውርደትና መሸማቀቅ ሊቆም ይገባል፡፡ የእናትና አባቶቻችንን፣ የእህትና ወንድሞቻችን በሙስሊምነታቸው የሚደርስባቸው እንባ ሊጠረግ ሊደርቅ ይገባል፡፡ ፊቶቻችን የምናያቸው እናትና አባቶች በሙስሊምነታቸው ሲደርስባቸው በነበረው ውርደት ምክንያት የተሰበረ ልባቸው ተጠግኖ፣ የተደፋው አንገታቸው ቀና ብሎ፣ በወለዱት ልጆች ተደስተው እየመረቁን ወደ አኼራ መሄድ አለባቸው፡፡ በአገራችን ሙስሊም መሆናችን ብቻ እንደ ሁለተኛ ደረጃ ዜጋ የምንቆጠርበት ጊዜ ሊያቆም ይገባል፡፡ አንገታችንን ቀና ማድረጊያው ጊዜ መቼም ሳይሆን አሁን ብቻ ስለሆነ መጅሊሱ ጠንካራ እንዲሆን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ይፈልጋሉ!!!

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on February 16, 2012 in Dimtsachin Yisema, Majlis

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: