RSS

መጅሊሱ እና አሕባሽ ላይ አገር አቀፍ ተቃውሞው ተፋፍሞ ቀጥሏል!!

16 Feb

የመጅሊስ ክስረት በአዲስ አበባ መስጂዶች!

የመጅሊስ ስብሰባዎች በህዝብ ተቃውሞ እየተበተኑ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜና እሁድ በአዲስ አበባ የተለያዩ መስጂዶች ከህዝብ ጋር ሊደረግ ታስቦ የነበረው ውይይት በአብዛኛው ሳይሳካ መቅረቱ ተሰማ፡፡ በስብሰባው አጀንዳ እንደተገለጸው ‹‹መጅሊስና አህባሽን አስመልክቶ የተፈጠሩ ብዥታዎችን የማጥራት አላማ አለው›› ተብሎ በብዙ የከተማችን መስጂዶች ተለጥፎ በነበረው ማስታወቂያ ቢገለጽም በተካሄዱት የሁሉም መስጂዶች ስብሰባ ግን መጅሊሱ ራሱ ትልቅ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ አመላካች ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ስብሰባው ከተካሄደባቸው መስጂዶች አንዱ ታላቁ አንዋር መስጂድ ነበር፡፡ በመስጂዱ የሴቶች መስገጃ አዳራሽ ውስጥ በተካሄደው በዚህ ስብሰባ በግምት ከ 250 እስከ 350 የሚደርሱ ሰዎች ተገኝተው ነበር፡፡ በመድረኩ ላይ የነበሩት ሁለት ሰዎች የመስጂዱ አሥተዳዳሪ እንዲሁም ኢማሙ ሐጂ ጧሃ ነበሩ፡፡ ኢማሙ ፕሮግራሙን በንግግራቸው በመክፈት ‹‹ስለሱፊያ እናስተምራችሁ›› ሲሉ የተደመጡ ሲሆን ይህንንም በማስተማር ላይ እያሉ ከተሳታፊዎች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡ ተሳታፊዎቹ ‹‹እኛ የመጣነው ስለሱፊያ ለመስማት ሳይሆን ስለአህባሽ ለማድመጥ ነው፤ እኛም ሱፊዮች ነን፤ እኛ ከሱፊያ ጋር ችግር የለብንም፤ በሰላምም አብረን እየኖርን ነው›› የሚል ጥያቄ ቢያነሱም ኢማሙ በገለጻቸው መቀጠሉን መርጠዋል፡፡ ይህ ያልጣማቸው በግምት ከተሳታፊዎቹ ሩብ የሚሆኑት ወጣትና አረጋዊ ተሰብሳቢዎች ‹‹ለጥያቄያችን ምላሽ ካልሰጡን ልናዳምጥዎት አንሻም!›› የሚል አጸፌታ ለኢማሙ በመስጠት በተክቢራ መስጊዱን ለቅቀው ወጥተዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ‹‹መጅሊስ ነጂስ! አህባሽ ይወገዳል!›› የሚል መፈክር ደጋግመው ያሰሙ ነበር – መስጂዱን ለቅቀው ሲወጡ ሐጂ ጧሃ መስጂዱን ለቅቀው የወጡትን ሰዎች ‹‹የዶሮ ጭንቅላት፣ መሃይማን›› ብለው ሲዘልፉ በጆሮዋችን አድምጠናል፡፡

ኢማሙ ከተቀሩት ተሰብሳቢዎች ጋር ስብሰባቸውን ለመቀጠል ቢጥሩም ሕዝቡ ‹‹ወደአህባሽ አጀንዳ ይግቡልን!›› በማለት ኢማሙን ሲያስጨንቃቸው ታይቷል፡፡ ተሰብሳቢዎቹ በድፍረት ‹‹ለምን ከውጪ አስተማሪዎች ማምጣት አስፈለገ? አገራችን በቂ አሊም የላትም ወይ? የመጅሊሱን ባለስልጣናት መቼ መረጥናቸው? አህባሽ አንድነታችንን እያደፈረሰው ስለመሆኑ አያምኑምን? መንግስት ለምን በሃይማኖታችን ጣልቃ ገባ?›› የሚሉ ጠጣር ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች ወደኢማሙ ቢሰነዝሩም ኢማሙ ጥያቄዎቹን አድበስብሰው ከማለፍ ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም፡፡ ‹‹ስልጠናው ሱፊያውን ማደራጀት ስላስፈለገ በጥናት ነው እየተሰራ ያለው›› የሚል ምላሽ በመስጠት የህዝቡን ቁጣ ለማርገብ ቢጥሩም ህዝቡ ግን በቁጣና በእልህ ‹‹ንግግሮትን መስማት አንፈልግም! እርስዎም አህባሽ ሆነዋል! አላሁ አክበር! መጅሊስ ነጂስ!›› ሲል ተሰምቷል፡፡ ፕግራሙ በዚያው የተቋረጠ ሲሆን ለመቋረጡ ዋነኛ ምክንያት የነበረውም ኢማሙ ጥያቄዎችን አልቀበልም ማለታቸው ነው፡፡ ይህም ህዝቡ በሞላ ቁጣው እንዲገነፍል ምክንያት ሆኗል፡፡

ፕሮግራሙ በዚህ መልኩ በክስረት ሲጠናቀቅ የመስጂዱ ኻዲሞች ኢማሙን ከበው ከመስጊዱ አውጥተዋቸዋል፡፡ የመድረኩ በዚያ መልኩ ያለውጤት መጠናቀቅ ግን ለኢማሙና ለመጅሊሱ ትልቅ ክስረት መሆኑን አመላካች ሆኗል፡፡ ምክንያቱም መጅሊስና ጀሌዎቹ አንዋር መስጂድን ዋነኛ የድጋፍ ማዕከላቸው አድርገው ሲመኩበት የቆዩ መሆኑና የህዝቡ ሁኔታ ግን በተቃራኒው ሆኖ መታየቱ ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ በፒያሳው ኑር መስጂድ፣ በሐጂ ዩኑስ መስጂድ፣ በፍልውሃ ተውፊቅ መስጂድ፣ በአኢሻ መስጂድ እና በቡራዩ ኩርቱ መስጂድ፣ በኮካ መስጊድ፣ በኮልፌ ኢማም ሐሰን መስጊድ፣ በአባጂፋር መስጊድ፣ በፈረንሳይ ለጋሲዮን መስጊድ፣ እንዲሁም በሰላሃዲን መስጊድ የተካሄዱ ስብሰባዎች በአንዋር መስጂድ አይነት ትዕይንቶች የተበተኑ ሲሆን የፍል ውሃው ተውፊቅ መስጂድ ግን አንድም ተሰብሳቢ ሳያገኝ ቀርቷል፡፡ የኑር (የበኒን) መስጂድ ምክትል ኢማምና የቢላል መስጂድ ዋና ኢማም በስብሰባው ከህዝብ አህባሽን አስመልክቶ በማስረጃ የቀረቡላቸው ጥያቄዎች መደናገጥ ውስጥ ከትተዋቸው ታይቷል፡፡ አቋማቸውን ለመለወጥ እና ከህዝብ ጋር አንድ ላይ ለመቆም ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ‹‹ጉዳዩ ይጣራም›› ብለዋል፡፡ የሁሉም መስጂድ ኢማሞች በመድረኮቹ ከመጅሊሱ በተሰጣቸው ትእዛዝ መሰረት የአህባሽን መልካምነት ለማስተማር እቅድ ይዘው የነበረ ሲሆን ሁሉም ሳይሳካ ስብሰባዎቹ በክስረት ተጠናቅቀዋል፡፡

በሌላም በኩል ረቡእ ምሽት በሬዲዮ ፋና በተዘጋጀ ፕሮግራም የውይይት ፕሮግራም ከመጅሊሱ ኡለማ ምክር ቤት የተወከሉ ሰዎች (ሐጂ ጣሃን ጨምሮ) ስለአህባሽ አስተምህሮ መልካምነት ደስኩረዋል፡፡ እየቀጠፉ የነበረው ሁሉ እንዳይጋለጥባቸው በመስጋትም የመረጡትን ጥያቄ ብቻ እያቀረቡ መልስ የሰጡ ለመምሰል የጣሩ ሲሆን ምንም አይነት ተከራካሪ በቀጥታ በድምጽ ጥያቄ እንዳያቀርብ አድርገዋል፡፡ ሐጂ ጣሃ ቅዳሜ በአንዋር መስጊድ አብደላ ሐረሪ ብዙ መክፈር የሌለባቸውን ዑለሞች ያከፈሩ መሆናቸውን በህዝብ ፊት አምነው የነበረ ቢሆንም በሬዲዮው ዝግጅት ግን ይህንን እውነታ ሙሉ በሙሉ ክደዋል፡፡

Advertisements
 
Leave a comment

Posted by on February 16, 2012 in Ahbash, Dimtsachin Yisema, Majlis

 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: